ከቡሌ ሆራ ዩኒቨርስቲ መጥተው በባህር ዳር ተጠልለው የቆዩት ተማሪዎች አካባቢውን ለቀው ወጡ

61

ባህርዳር  ጥር 8/2011 በነበረው የፀጥታ ችግር ምክንያት  ከቡሌ ሆራ ዩኒቨርስቲ መጥተው በባህዳር ተጠልለው የቆዩት ተማሪዎች ዛሬ  ከተማዋን ለቀው መውጣታቸውን የክልሉ ሰላም ግንባታና የህዝብ ደህንነት ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ገደቤ ኃይሉ ለኢዜአ እንደገለጹት ተማሪዎቹ በባህር ዳር ከተማ  ህብረተሰብ  ላለፉት ሁለት ሳምንታት ተገቢው ድጋፍና እንክብካቤ ሲደረግላቸው ቆይቷል።

ሆኖም  ባለፉት ሁለት ቀናት ተጠልለውበት ከሚገኙት ብሄራዊ ስታዲየም በመውጣት በከተማው ሁከትና ብጥብጥ መፍጠራቸውን አስታውሰዋል።

በተፈጠረው ችግርም የከተማው ህዝብ ሰላምና ደህንነት መታወኩን ጠቅሰው፤ ህብረተሰቡ የአልባሳትም ሆነ የምግብ ድጋፍ እያደረገ ብጥብጥ መፍጠሩ ተገቢ ባለመሆኑ ትናንት ከተማዋን ለቀው እንዲወጡ ማሳሰቢያ ተሰጥቶ እንደነበር አመልክተዋል።

በተሰጠው ማሳሰቢያ መሰረትም ዛሬ የቀረበላቸውን ወደ ዩኒቨርስቲው ተመልሶ የመማር አማራጭ የተቀበሉ 45 የሚበልጡ ተማሪዎች ትራንስፖርት፣ የአልባሳትና መሰል ድጋፍ ተመቻችቶላቸው እንዲመለሱ ተደርጓል።

ወደ ዩኒቨርስቲው ከተመለሱት ተማሪዎች ጋርም የከተማው ሰላም አስከባሪ ወጣቶችና አመራር አብሯቸው መጓዙን አቶ ገደቤ አስታውቀዋል።

ሌሎች ተማሪዎች ከተማዋን አንለቅም እንቆያለን ቢሉም የከተማው ወጣት ከዚህ በላይ መታገስ አንችልም በሚል በተደረገባቸው ግፊት ወደ የቤተሰቦቻቸው መመለሳቸውን ገልጸዋል።

ከተማዋ ዛሬ የተረጋጋ ሰላም መዋሉን ጠቅሰው፤  የጥምቀት በዓልም በሰላማዊ ሁኔታ ለማክበር ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን አመልክተዋል፡፡

በነበረው የፀጥታ ችግር ከቡሌ ሆራ ዩኒቨርስቲ  መጥተው  በባህር ዳር ብሄራዊ ስታዲየም ተጠልለው የቆዩት ተማሪዎች  ከ2500 በላይ እንደሆኑም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም