የሚኒስቴሩና ተጠሪ ተቋማቱ ከ90 ሚሊዮን ብር በላይ ያልተወራረዱ ተሰብሳቢ ሂሳቦች በኦዲት ግኝት ተረጋግጠዋል

945

አዲስ አበባ   ጥር 8/2011 በቀድሞ የእርሻና ተፈጥሮ ሐብት ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማቱ ከ90 ሚሊዮን ብር በላይ ያልተወራረዱ ተሰብሳቢ ሂሳቦችና ከ26 ሚሊዮን ብር በላይ ሳይከፈሉ የቆዩ ተከፋይ ሂሳቦች መኖራቸው በኦዲት ግኝት ተረጋግጧል።     

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም ሚኒስቴሩ ከህግና መመሪያ ውጭ የተፈጸሙ የኦዲት ጉድለቶችን ለማረም የሚለካ ውጤት ማስመዝገብ እንዳለበት አሳስቧል።    

የምክር ቤቱ የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በቀድሞ የእርሻና ተፈጥሮ ሐብት ሚኒስቴር የ2009 በጀት ዓመት የኦዲት ግኝት ላይ ከሚኒስቴሩ የሥራ ኃላፊዎች ጋር ተወያይቷል።           

በውይይቱ ላይ በሚኒስቴሩ የተገዙና በእርዳታ የገቡ ግምታቸው ከ105 ሚሊዮን ብር በላይ የሆኑ ዕቃዎች ገቢ የተደረጉበት የንብረት ገቢ ደረሰኝ እንዳልተያያዘም ተገልጿል።  

ቋሚ ኮሚቴው በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱና ተጠሪ ተቋማቱ የታየውን የኦዲት ግኝት ለማረምና ሊለካ የሚችል ውጤት ለማስመዝገብ መስራት እንደሚጠበቅባቸው ነው ያሳሰበው።     

ሚኒስቴሩ የታዩ ጉድለቶችን በዕቅድ ለመፍታት ጥረት ማድረግ እንዳለበት ያስገነዘበው ቋሚ ኮሚቴው የተከናወኑና ያልተከናወኑ ተግባራትን ከነምክንያታቸው በማስቀመጥ በወቅቱ ሪፖርት እንዲያደርግም አሳስቧል።   

ሚኒስቴሩ የመንግስትና የህዝብ ሐብት በአግባቡ በማስተዳደርና ጥቅም ላይ በማዋል በወቅቱ ገቢ መደረግ ያለባቸውን ሂሳቦች በአስቸኳይ ገቢ እንዲያደርግም ትዕዛዝ ሰጥቷል። 

ኃብትን በአግባቡ ለማስተዳደር የውስጥ ኦዲትን ማጠናከርና የሰው ኃይሉን በቁጥርም ሆነ በአቅም ማሳደግ እንዳለበትም ቋሚ ኮሚቴው አመላክቷል።

ሚኒስቴሩ የኦዲት ግኝቱን ለማስተካከል የጀመራቸው ተግባራት አበረታች መሆናቸውን የገለጸው ቋሚ ኮሚቴው ጅምሩ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም አስገንዝቧል።      

የግብርና ሚኒስትሩ ዑመር ሁሴን ለቋሚ ኮሚቴው በሰጡት ምላሽ ከኦዲት ግኝቱ በኋላ በተከናወኑ ተግባራት ከተሰብሳቢ ሂሳብ ከ12 ሚሊዮን ብር በላይና ከተከፋይ ሂሳቦችም 21 ሚሊዮን ብር መወራረዱን ገልጸዋል።   

ሰነዶቹ በሚገባ ያልተደራጁ በመሆናቸውና ቀደም ሲል ቦታው ላይ የነበሩ ሰዎች ባለመኖራቸው ለማደራጀት ጊዜ መውሰዱንና የኦዲት ግኝቱን በፍጥነት ለማከናወን መቸገራቸውን አስረድተዋል።        

ያም ሆኖ በቋሚ ኮሚቴው የተነሱ ሐሳቦች በቀጣይ ለሚከናወኑ ተግባራት ግብዓት እንደሚሆኑ ነው የተናገሩት።    

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ምክትል ዋና ኦዲተር ወይዘሮ መሰረት ዳምጤ በበኩላቸው ሚኒስቴሩ በኦዲት የተገኙበትን ጉድለቶች ለማስተካከል የውስጥ ኦዲተሩንና የሰው ኃይሉን ማጠናከር እንዳለበት ተናግረዋል።  

መስሪያ ቤታቸው ሚኒስቴሩ በ2009 በጀት ዓመት የታየበትን የኦዲት ግኝት ለማስተካከል በሚከውናቸው ተግባራት የሚመጡ ለውጦችን እያካሄደ ባለው የ2010 በጀት ዓመት ኦዲት እንደሚያረጋግጥም አስታውቀዋል።