በምዕራብ ሸዋ ከ10 አመት በላይ ያለስራ ተከልሎ የተቀመጠ መሬት ተመላሽ ተደረገ

114

አምቦ ጥር 8/2011 በምዕራብ ሸዋ ዞን ኢሉ ገላንና ደንዲ ወረዳዎች  በኢንቨስትመንት ስም ተወስዶ ከአስር  ዓመታት በላይ  ሳይለማ የቆየ መሬት ወደ መንግስት እንዲመለስ ተደረገ፡፡

ኢሉ ገላን ወረዳ የገጠር መሬት ልማት ማኔጅመንት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሌሊሳ ከበደ እንደገለጹት ለኢንቨስትመንት መሬት ወስደው ያለልማት ባስቀመጡ ባለሃብቶች ላይ 92 ሄክታር መሬት ወደ  መሬት ባንክ ገቢ ሆኗል ፡፡

ባለሀብቶቹ በልማት ስም የወሰዱትን መሬት ከአስር ዓመታት በላይ ያለ ጥቅም ከልለው ማስቀመጣቸው በህብረተሰቡ ዘንድ የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ሆኖ መቆየቱን አስረድተዋል፡፡

" አሁን ከባለሃብቶቹ የተመለሰው መሬት ላይ ወጣቶችን በማደራጀት የስራ አጥነት ችግር ለመፍታት እንጠቀምበታለን" ብለዋል ።

በተመሳሳይ በደንዲ ወረዳ 2 ነጥብ 8 ሄክታር መሬት ያለ ልማት ታጥሮ በመቀመጡ  ተመላሽ መደረጉን የወረዳው መሬት ልማት ማኔጅመንት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ከበደ ኃይሉ ተናግረዋል፡፡

መሬቱ ለቱሪዝም ልማት በሚል ከሰባት ዓመታት በፊት በአንድ ባለሀብት የተወሰደ እንደነበር ያስታወሱ ኃላፊው የተመለሰውም ለመምህራን የቤት መስሪያ ቦታ እንደሚውል አስታውቀዋል፡፡       

በኢሉ ገላን ወረዳ የኢጃጂ ከተማ ነዋሪ አቶ ጌታቸው ታደሠ በሰጡት አስተያየትም መንግስት ይህን መሰል እርምጃ መውሰድ መጀመሩ የሚበረታታ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በርካታ ስራ አጥ ወጣቶች ባሉበት ወረዳ ባለሃብቶች ያለ ልማት መሬት አጥረው ማስቀመጥ ተገቢ ባለመሆኑ በመንግስት በኩል የተወሰደው እርምጃ የህዝቡን የመልካም አስተዳደር ጥያቄ የመለሰ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

"የተወሰደው መሬት የማስመለስ ተግባር የዘገየ ቢሆንም ተገቢነቱ ግን አጠራጣሪ አይደለም" ያሉት ደግሞ በደንዲ ወረዳ ጊንጪ ከተማ ነዋሪ አቶ ጋዲሣ አመንቴ ናቸው፡፡ 

አሁንም አለአግባብ ተከልለው የተቀመጡ ቦታዎች ስላሉ እርምጃው ተጠናክሮ እንዲቀጥል አቶ ጋዲሳ ጠቁመዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም