የሀሸንገ ሀይቅን ከጥፋት የሚታደግ ፕሮጀክት እንደሚካሄድ ተገለጸ

ማይጨው ጥር 8/2011 የሀሸንገ ሀይቅ ከጥፋት ለመታደግ የሚያስችል  የልማት ፕሮጀክት እንደሚካሄድ የትግራይ ክልል ግብርናና ገጠር ልማት ቢሮ ገለጸ፡፡ 

በሀይቁ እያጋጠሙት ያሉት ተግዳሮቶችና የመፍትሄ አቅጣጫዎች ዙሪያ  በኮረም ከተማ ውይይት ተካሂደዋል፡፡

የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ክፍሎም አባዲ በውይይት ወቅት እንደገለጹት የሀሸንገ ሀይቅ ለረጅም ጊዜ በደለል እየተሞላ ለአደጋ ተጋልጧል፡፡

ሀይቁ ከተጋረጠበት የጥፋት አደጋ  ለመታደግ የሚያስችል የልማት ፕሮጀክት ከመጪው የካቲት ወር ጀምሮ  እንደሚካሄድ ተናግረዋል፡፡

በሀይቁ ዙሪያ የሚገኝ ከ8ሺህ በላይ ሄክታር መሬት የመከላካያ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ በማከናወን ደለልን  መከላከል የፕሮጀክቱ አንዱ የመፍትሄ አቅጣጫ  መሆኑን  አቶ ክፍሎም አመልክተዋል፡፡

ለዚህም  የክልሉ መንግስት ስድስት ሚሊዮን 500ሺህ  ብር በጀት መመደቡን ገልጸው በበጀቱ ከሚከናወኑት የአፈርና ውሃ ጥበቃ ተግባራት መካከል በጎርፍ የተቦረቦረ ስፍራዎችን ማዳንና  የእርከን ስራዎችን ጠቅሰዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የተቦረበሩ ስፍራዎችን ለማልማት የሚያግዝ  የብረት ሽቦ ወደ አካባቢው መግባቱን ጠቁመው በሀይቁ ዙሪያ የሚገኙ የስምንት ቀበሌ ገበሬ ማህበርራት አርሶአደሮች የሃያ ቀናት ነጻ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ላይ እንደሚሳተፉ ተናግረዋል፡፡

"በተፈጥሮ ሃብት ልማት ዘርፍ የሚንቀሳቀሱ ሀገር በቀልና የውጪ ድርጅቶችን በማስተባበር ለቀጣይ ሶስት ዓመታት የሚቀጥል ሀይቁን የማዳን ስራ ይከናወናል" ብለዋል፡፡

የቢሮው ምክትል ኃላፊው እንዳሉት በሀይቁ ውስጥ የሚገኘውን የዓሳ ሃብት ከጥፋት ለመጠበቅ ውሃውን የማከም ተግባር ሌላው የፕሮጀክቱ አካል ነው፤ ይህም የሀይቁ ዓሳ ሃብት እርባታን በማሻሻል የአካባቢው አርሶአደሮች ከዘርፉ ልማት የተሻለ ተጠቃሚ ለማድረግ ያስችላል፡፡

በሀይቁ ዙሪያ ለኢንቨስትመንትና ለቱሪዝም እንቅስቃሴ በማመቻቸት የአካባቢው ነዋሪዎች የስራ እድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ እንደሚመቻቸም ተነልክቷል፡፡

የሀሸንገ ሀይቅ በ2006 ዓ.ም. ውሃው  1ሺህ 549 ሄክታር መሬት ይሸፍን የነበረው  አሁን ወደ 13 ሄክታር ዝቅ ማለቱን በጥናት ማረጋገጣቸውን የገለጹት ደግሞ በክልሉ ሀብት ቢሮ የተፋሰስ ልማት ባለሙያ አቶ አለሙ ገብረመድህን ናቸው፡፡

በሀይቁ ዙሪያ ከሚገኙ 23 ከፍተኛና አነስተኛ ሸለቆዎች በየዓመቱ አራት ሺህ ኩንታል ደለል ወደ ሀይቁ በጎርፍ አማካኝነት ይገባል፡፡

በአካባቢው  የእርሻ መሬትና ልቅ ግጦሽ እየተስፋፋ በመምጣት ሀይቁ ለደለል መሞላትና የደን ሃብት መመናመኑን  ባለሙያው ያመለከቱት ሌላው ምክንያት ነው፡፡

በሀይቁ ዙሪያ የእርሻ ስራ የሚያከናውኑ አርሶ አደሮች በሌላ የገቢ ምንጭ እንዲተዳደሩ ማድረግ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም በመፍትሄነት ጠቁመዋል፡፡

ሀይቁን ለመታደግ ቢዘገይም አሁን ትኩረት መሰጠቱ   የሚበረታታ መሆኑን የሀሸንገ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ነዋሪ አርሶ አደር ሀጎስ ያሲን በሰጡት አስተያየት ገልጸዋል፡፡

በተፈጥሮ ሃብት ልማቱ ስራ በጉልበት በመሳተፍ ድጋፋቸውን ለመስጠት ዝግጁ መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡

ሌላው የቀበሌው ነዋሪ  አቶ ንጉስ አምባው በበኩላቸው በሓሸንገ ሓይቅን ዙሪያ የሚካሄዱ የልማት ስራዎች የአካባቢው ህዝብ የሚጠቅም በመሆኑም በጉልበት እንደሚሳተፉ ተናግረዋል፡፡

የሀሸንገ ሀይቅ ለጥፋት መጋለጡን አርሶ አደሮችና የመቀሌ ዩኒቨርስቲ ምሁራን በምንጭነት ጠቅሶ ኢዜአ  ከዚህ በፊት መዘገቡ ይታወቃል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም