የፋይናንስ አቅርቦት እጥረት በመኖሩ ምክንያት የግንባታው ዘርፍ ተቀዛቅዟል

104
አዲስ አበባ ግንቦት 18/2010 የፋይናንስ አቅርቦት እጥረት በመኖሩ ምክንያት የግንባታው ዘርፍ መቀዛቀዝ ማሳየቱን የዘርፉ ባለድርሻ አካላት ገለጹ። "ባንኮችና ኢንሹራስ ኩባንያዎች ለዘላቂ የግንባታ ኢንዱስትሪ እድገት ያላቸው ሚና" በሚል መሪ ሀሳብ የኢትዮጵያ ሲቪል መሐንዲሶች ማህበር ያዘጋጀው ስብሰባ ዛሬ በአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን መሰብሰቢያ አዳራሽ ተካሄዷል። በመድረኩም የፋይናንስ አካላት አሁን ያለውን ጉዳይ ትልቅ ትኩረት በመስጠት ለአገሪቷ ኢኮኖሚ ወሳኝ ሚና እየተወጣ ላለው የግንባታው ዘርፍ የፋይናንስ አቅርቦት እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል። የፍሊንት ስቶን ኢንጂነሪንግ ኤንድ ሆምስ ድርጅት ዋና ስራ አስፈጻሚ ኢንጂነር ፀደቀ ይሁኔ "ለግንባታው ዘርፍ  ለስራ ማስኬጃና ለማሽነሪም የሚሆን የፋይናንስ አቅርቦት እጥረት እንዳለና በተለይ በዚህ ዓመት ችግሩ በስፋት መታየቱን" ይገልጻሉ። የፋይናንስ ተቋማት የሚለቁት ገንዘብ ማነሱ ብቻ ሳይሆን የውጭ ምንዛሬ አለመኖሩ የግንባታ ስራዎች በተቀመጠላቸው ጊዜ እንዳይከናወኑ እያደረገ እንደሆነም ነው የሚገልጹት። የሕብረት ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበርና ባለሀብት አቶ ዛፉ እየሱስወርቅም ለግንባታው ዘርፍ መቀዛቀዝ ምክንያት የፋይናንስ አቅርቦት ችግር ነው በሚለው ሀሳብ እንደሚስማሙ ገልጸዋል። ያም ቢሆን ለግንባታው ዘርፍ ጨርሶ ገንዘብ የለም ሳይሆን በዘርፉ የሚፈለገው የፋይናንስ አቅርቦት አለመኖር የትኩረት አቅጣጫው ወደ ኤክስፖርትና አምራች ዘርፉ መዞሩ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ነው የሚናገሩት። ባንኮችና ሌሎች የፋይናንስ ተቋማት የተትረፈረፈ ሳይሆን የተመጠነ ሀብት እንዳላቸው ገልጸው በተቻለቸው አቅምም ለግንባታው ዘርፍ የሚችሉትን ድጋፍ እያደረጉ ነው ብለዋል። ከዛሬው መድረክ ባለፈ የግንባታና የፋይናንስ ተቋማት በጥልቀት በመወያያትና ያሉትን ችግሮች በስፋት በመገምገም ለዘላቂ መፍትሔ በጋራ መስራት እንዳለባቸውም አመልክተዋል። "የግንባታው ዘርፍ ኢንዱስትሪ ከፍተኛ የካፒታልና የመሳሪያዎች አቅም የሚጠይቅ የስራ ዘርፍ ነው" የሚሉት ደግሞ የኮንስትራክሽን ሚኒስትሯ ኢንጂነር አይሻ መሐመድ ናቸው። በዘርፉ ያለውን የፋይናንስና ሌሎች ችግሮችን ለመፍታት መንግስት የዘርፉ የ10 ዓመት የአቅም ግንባታ መርሃ ግብር ቀርጾ እየሰራ መሆኑን ነው ያስረዱት። የፋይናንስ ችግር በግንባታው ዘርፍ ከሚጠቀሱ ዋነኛ ችግሮች አንዱ መሆኑን በመለየት ችግሩን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ሆኖ ለመፍታት ጥረት እየተደረገ ነውም ብለዋል። በግንባታው ዘርፍ ላይ ያሉ በፋይናንስ፣ በጥራትና በፕሮጀክቶች መጓተትና ሌሎች ችግሮችና የአሰራር ጉድለቶችን በማስተካከል ኢትዮጵያ በዘርፉ ያላትን ተጠቃሚነትና አቅም ማሳደግ በይበልጥ የሚሰራበት ጉዳይ እንደሆነም ሚኒስትሯ ገልጸዋል። የግንባታው ዘርፍ የላቀ ስኬትና ተወዳዳሪነት እንዲኖረው መንግስት እያደረገ ካለው ጥረት በተጨማሪ የፋይናንስ ተቋማት አመራሮች፣ የዘርፉ ተዋናዮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በቁርጠኛነት፣ በጽናትና በቅንጅት መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል። በስብሰባው ላይ "ባንኮችና ኢንሹራስ ኩባንያዎች ለዘላቂ የግንባታ ኢንዱስትሪ እድገት ያላቸው ሚና" በሚል ሁለት የመወያያ ጽሁፎች ቀርበው በተሳታፊዎች ውይይት ተደርጎባቸዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም