ያልተጠቀምንበት ሀብት

1386

ምናሴ ያደሳ(ኢዜአ)

አርሶአደር ታሪኩ ቶለሳ በኢሉአባቦር ዞን ያዮ ወረዳ ጌሪ ቀበሌ ከመደበኛው የግብርና ልማት በተጓዳኝ ንብ በማነብ ኑሮዋቸውን ይገፋሉ፡፡

ከአርሶአደሩ ጋር በነበረኝ ቆይታ እንደነገሩኝ አካባቢያቸው አመቱን በሙሉ በሚያብቡ የተፈጥሮ ዛፍ አይነቶች የተሞላ በመሆኑ ለልማቱ አመቺ ሁኔታ ፈጥሮላቸዋል፡፡ በአመት እስከ ሶስት ጊዜ በታህሳስ፣ መጋቢትና ሰኔ ወራት ማር በመቁረጥ ለገበያ እያቀረቡ ነው፡፡

“ንብ ማነብ የጀመርኩት የዛሬ አስር አመት ገደማ ነው” ያሉት አርሶአደሩ  ሲጀምሩ ከነበረው ከአንድ ሺህ ብር የማይበልጥ ገቢ ከሁለት አመታት ወዲህ በየአመቱ  ምርቱን ለገበያ በማቅረብ ከ300 ሺህ ብር በላይ  እያገኙ ነው፡፡

ከአምስት አመታት በፊት  ልማቱን የሚያካሄዱት ባህላዊ ቀፎ ብቻ በመጠቀም ነበር፡፡ ይህም ቀፎውን ሲሰቅሉና  ማር ሲቆርጡ ከነበረው አድካሚነት በተጨማሪ የሚያገኙት ምርት አነስተኛ ነበር፡፡

 ባህላዊ ቀፎ ለንቦች እምብዛም ተስማሚነት ስለሌለው ንቦች እንደገቡ የሚወጡበት አጋጣሚም ብዙ እንደ ነበር ነው የሚናገሩት፡፡

አርሶአደሩ በአሁኑ ወቅት በአብዛኛው ልማቱን የሚያካሄዱት ተሸጋጋሪና ዘመናዊ ቀፎዎችን በመጠቀም ነው፡፡ ባህላዊ ቀፎ ንቦችን ወደ ዘመናዊ ቀፎ ለማሸጋገርና ለሰም ምርት ስለሚጠቅማቸው ሙሉ ለሙሉ  መጠቀም እንዳላቆሙ ነው የገለጹት፡፡

“በአሁኑ ወቅት 50 ባህላዊና መቶ ያህል ተሸጋጋሪና ዘመናዊ ቀፎ በመጠቀም እያለማሁ ነው” ያሉት አርሶአደር ታሪኩ ባለፈው አመት ከ60 ተሸጋጋሪና ዘመናዊ ቀፎዎች ብቻ ከ3 ሺህ ኪሎግራም በላይ ምርት በማሰባሰብ ለገበያ አቅርበዋል፡፡

የሚሰበስቡትን የማር ምርት ንቦቹ በሚቀስሙት የዛፍ አበባ አይነት ለይተው እንደሚያስቀምጡና ይህም በጥራትና በተፈጥሮአዊነት የተሻለ በመሆኑ ገበያ እየሳበላቸው መምጣቱን ተናግረዋል ፡፡

ምርቱን በአካባቢያቸው ገበያ  አንዱን ኪሎ ግራም በ150 ብር በተለያዩ ሀገራዊ ባዛሮች ተጋብዘው ደግሞ እስከ 300 ብር መሸጥ ችለዋል፡፡ በውጤታማነታቸውም እስከ ክልል ደረጃ እውቅናና የምስክር ወረቀት እንዳገኙ ገልጸዋል፡፡

አካባቢያቸው ካለው ተስማሚነት የተነሳ በሰሩት ልክ ምርት ማግኘት እንደሚችሉ የተናገሩት አርሶአደር ታሪኩ  ይህ ግንዛቤ በሁሉም አርሶአደሮች ዘንድ ያለመዳበሩ እንደ ችግር የሚታይ ነው ብለዋል፡፡

ልምዳቸውን ለሌሎች አርሶአደሮች በማካፈል ምርታማነቱን ለማሳደግ እየሰሩ እንደሆነም ያብራራሉ፡፡

በኢሉአባቦር ዞን የተለያዩ ወረዳዎች ለመታዘብ እንደሚቻለው አብዛኛው አርሶአደር የንብ ማነብ ስራውን የሚያከናውነው ከሳርና ከሀረግ በመሳሰሉ ነገሮች  ባህላዊ ቀፎዎችን ሰርተው ረጃጅም እንጨቶች ላይ በመስቀል ነው፡፡ ይህንንም የሚያደርጉት ዛፎቹ ላይ በመውጣት ለመስቀል አቅም ያለው ቤተሰብ ወይም አርሶአደሮች ናቸው፡፡

ባህላዊ ቀፎዎች ከሚሰሩበት ቁሳቁስ ጥንካሬ አነስተኛ መሆን የተነሳ ከአንድ አመት በላይ አያገለግሉም፡፡ ቀፎዎቹን ለመስቀል በሚደረግ ጥረትም አልፎ አልፎ ከእንጨት ላይ በመውደቅ የሚጎዱ ሰዎች አሉ፡፡

በዞኑ መቱ ወረዳ ቡሩሳ ቀበሌ አርሶአደር ረጋሳ ሂካ  ከ30 አመታት በላይ በባህላዊ ቀፎ ንብ ማነብ ስራ ተሰማርተዋል፡፡ ቀፎዎቹን በመስቀልና በማውረድ በሚያደርጉት ጥረትም ከሶስት ጊዜ በላይ ከዛፍ ላይ ወድቀው ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ ከድካሙም ባለፈ የሚያገኙት ምርት መጠን አነስተኛ ነበር ።

ካለፉት ሶስት አመታት ወዲህ ግን ከአካባቢያቸው የዛፍ ውጤቶች የሚያዘጋጁትን ተሸጋጋሪ ቀፎዎችና ከመንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች  በብድር የቀረበላቸውን  15 ቀፎዎች በመጠቀም ድካም ቀንሰው የተሻለ ምርት መሰብሰብ ጀምረዋል፡፡

“ዘመናዊ ቀፎዎቹ በብድር የምናገኘው በሶስት አመታት ተከፍሎ በሚጠናቀቅ  ነው” ያሉት አርሶአደሩ  ይህም የሚሰበስቡትን የማር ምርት ለገበያ በማቅረብ በወቅቱ ከፍለው ለማጠናቀቅ እንደረዳቸው ተናግረዋል፡፡ ባለፈው አመት ከ500 ኪሎግራም በላይ ምርት በማሰባሰብ ለገበያ አቅርበው ከ90 ሺህ ብር በላይ ገቢ አግኝተዋል፡፡

በዘመናዊ እና ባህላዊ ቀፎ አጠቃቀም ዙሪያ በቂ ስልጠና በማግኘታቸውም በየአመቱ ምርታማነታቸውን ለማሳደግ ትኩረት ሰጥተው እየሰሩ ነው፡፡ በመስኩ በከፍተኛ ደረጃ ውጤታማ የሆኑ አርሶአደሮችም ስለ ተሸጋጋሪ ቀፎ አሰራር ስልጠና በመስጠትና ቀፎዎቹን በሽያጭ በማቅረብ እያገዟቸው እንደሆነ ነው አርሶአደሩ የሚናገሩት፡፡

ባላቸው ሙያና ልምድ ከአካባቢው የእንጨት ውጤቶች ተሸጋጋሪ ቀፎ በማዘጋጀት ለአርሶአደሮች ሙያቸውን እያጋሩ ካሉት መካከል በበቾ ወረዳ በቾ ቀበሌ ነዋሪ አቶ  መሀመድ ፍሰሀ አንዱ ናቸው፡፡

አርሶአደሩ እንዳሉት በዚህ ተግባራቸው በሀገር አቀፍ ደረጃ የእውቅናና ምስጋና ምስክር ወረቀት አግኝተዋል፡፡ በሆለታ ግብርና ምርምር ማዕከል ተጋብዘውም የሙያና ቁሳቁስ ድጋፍ አግኝተዋል፡፡

“በግሌ ከተለያዩ የዛፍ ውጤቶች ያዘጋጀሁትን ከ100 በላይ ዘመናዊና ቀፎ በመጠቀም ልማቱን እያካሄድኩ ነው” የሚሉት አርሶአደሩ ለአካባቢው ወጣቶችም በተሸጋጋሪ ቀፎ አዘገጃጀት እና በአመራረቱ ዙርያ የሙያ እገዛ እያደረጉ መሆኑን ይናገራሉ፡፡

ከአንድ ቀፎ በየአመቱ እስከ 40 ኪሎግራም የማር ምርት እያገኙ ነው ፡፡ በወረዳው ርዕሰ ከተማ በቾ ላይም ቤት በመገንባት በንግድ ስራ ተሰማርተዋል፡፡ አርሶአደሩ እንዳሉት  የንብ ማነብ ስራ እንደሌላው የግብርና መስክ ብዙ ድካም ስለሌለው ልማቱን በይበልጥ ለማስፋፋት እየሰሩ ነው፡፡

የኢሉአባቦር ዞን ካለው ተፈጥሮ ሀብቱ እና ለማር ምርት አመቺነት አንጻር ሲታይ የሚመረተው ምርት አባይን በጭልፋ እንደማለት ነው፡፡ ዞኑ ካለው ከአንድ ሚሊዮን ሄክታር ስፋት ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆነው በደን የተሸፈነ ነው፡፡ በዚህ የደን ክልል ውስጥ ደግሞ ክረምት ከበጋ የሚያብቡና ንቦች የሚቀሱሟቸው በርካታ ሀገር በቀል የዛፍ ዝርያዎች ይገኛሉ፡፡

አመቺነቱ በመጠቀምም ከዞኑ በየአመቱ እስከ 30 ሺህ ሜትሪክ ቶን የማር ምርት መሰብሰብ ቢቻልም በአሁኑ ወቅት እየተሰበሰበ ያለው አመታዊ ምርት ከ5 ሺህ ሜትሪክ ቶን እንደማይበልጥ ከዞኑ እንስሳት ሀብት ልማትና ጤና ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመላክታል ፡፡

በዞኑ የማር ምርታማነት መጠን ከአቅም በታች ከሆነባቸው ምክንያቶች መካከል አርሶአደሮች ልማቱን የሚያካሄዱት  አነስተኛ ምርት የሚሰጡ ባህላዊ ቀፎዎችን በመጠቀማቸው ነው ።

በልማቱ  የሚሳተፉ አርሶአደሮች ቁጥር አነስተኛ መሆን ሌላው ምክንያት መሆኑን የዞኑ እንስሳት ሀብት ልማትና ጤና ጽህፈት ቤት ሀላፊ ዶክተር ተሬሳ ፈዬራ  ይገልፃሉ ፡፡

ካለፉት አምስት ሶስት አመታት ወዲህ አርሶአደሩ በዘመናዊ  እና ተሸጋጋሪ ቀፎዎች በመጠቀም ምርታማነቱን እንዲያሳድግ  መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በመተባበር በኤክስቴንሽን መርሀግብር  የሙያ ስልጠና የመስጠትና ዘመናዊና ተሸጋጋሪ ቀፎዎችን የማላመድ ስራዎች እየተሰሩ ነው፡፡

በኤክስቴንሽን መርሀግብሩም በዞኑ 13 ወረዳዎች ከሶስት አመታት በፊት በአርሶአደሮች ጥቅም ላይ ሲውል የነበረውን  16 ሺህ 500  ዘመናዊ ቀፎ አሁን ላይ ወደ 35 ሺ 200 ለማሳደግ ተችሏል ፡፡

አርሶአደሩ በቀላሉ ከአካባቢው የዛፍ ውጤቶች በማዘጋጀት እንዲጠቀም በተሰጠው የሙያ ድጋፍና ትምህርት የተሸጋጋሪ ቀፎዎችን ቁጥርም ከ50 ሺህ ወደ 157 ሺህ ለማሳደግ ተችሏል፡፡ በተሸጋጋሪ ቀፎ አዘገጃጀት የተሻለ ውጤት ያሳዩ አርሶአደሮችም በተለያዩ ወረዳዎች በመዘዋወር ለሌሎች ልምዳቸውን እንዲያካፍሉ እየተደረገ ነው፡፡

ሀላፊው እንዳሉት ባለፈው አመት በተለይ የበለጠ ተስማሚነት ባላቸው የበቾ፣ ያዮ፣ አልጌ፣ቢሎኖጳ፣ዲዱ እና ሰሌኖኖ ወረዳዎች በመስኩ ለተሰማሩ ከ3 ሺህ 300 በላይ አርሶአደሮች ተጨማሪ የሙያ ስልጠና እና የምርት ቁሳቁሶችን በማቅረብ ለራሳቸው ውጤታማ እንዲሆኑና ለሌሎች አርሶአደሮችም የሙያ ድጋፍ በማድረግ ወደ ልማቱ እንዲገቡ መደረጉንም ገልጸዋል፡፡

ለአርሶአደሩ ዘመናዊ ቀፎዎችን በረጅም ጊዜ ብድርና በድጋፍ በማቅረብ ዘመናዊ አመራረቱን ለማላመድ  እየተሰራ ባለው ስራ የማር ምርታማነት እንዲያድግ እያደረገ ነው፡፡

ባለፈው አመት በዞኑ 5 ሺህ 700 ሜትሪክ ቶን  የማር ምርት የተሰበሰበ ሲሆን ይህም ከቀዳሚው አመት ጋር ሲነፃፀር ከ900 ሜትሪክ ቶን በላይ ብልጫ አለው፡፡

በዚህ አመትም ከ38 ሺ900 በላይ  ዘመናዊ ቀፎዎች  ለአርሶአደሮቹ ተሰራጭቷል ። በዚህም እስከ አመቱ ማጠናቀቂያ ድረስ ከ6 ሺህ ሜትሪክ ቶን በላይ  የማር ምርት ለማሰባሰብ ታቅዶ እየተሰራ ነው  ፡፡

የኢሉአባቦር ዞን ካለው ተፈጥሯዊ ይዘቱ የተነሳ መመረት የሚገባውን የማር ምርት መጠን ለማምረት በመስኩ ለተሰማሩ አርሶአደሮች እየተደረገ ያለው ድጋፍ ዘግይቶ የጀመረ ቢሆንም አሁን በሚታየው መልኩ ተጠናክሮ ከቀጠለ የአርሶአደሩን ኢኮኖሚ አቅም በማሳደግና ለሀገሪቱ የውጪ ምንዛሪ ማደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ባይ ናቸው ፡፡

ፈጠራን የሚያበረታቱ አሰራሮችን በመከተል በራሳቸው ተነሳሽነት ከአካባቢያቸው ዘመናዊ ቀፎዎችን አዘጋጅተው የሚጠቀሙ አርሶአደሮች ክህሎታቸውን እንዲያስፋፉም የበለጠ ሊሰራ ይገባል፡፡

በኢሉአባቦር ዞን 13 ወረዳዎች ከሚገኙ አርሶአደሮች ከመደበኛ ግብርና ልማት በተጓዳኝ በንብ ማነብ ተሰማርተው ተጠቃሚ በመሆን የቻሉት  34 ከመቶ የሚሆኑት ብቻ ናቸው፡፡ ይህ የሚያመላክተው አርሶአደሩ በዙርያው በቀላሉ መጠቀም የሚገባውን እያገኘ እንዳልሆነ ነው፡፡

የንብ ማነብ ተግባር በመደበኛነት ከሚከናወኑ የግብርና ልማት ስራዎች ከሚገኘው ገቢ ቢበልጥ እንጂ አያንስም ፡፡ ስራውም እንደሌሎች የልማት መስኮች ሙሉ ጊዜ የሚወስድና አድካሚ አይደለም፡፡ አርሶአደሩ ይሄንን ጠቀሜታ በመረዳት ከየትኛውም የልማት ስራ በተጓዳኝ ማር በማምረት ኢኮኖሚያዊ አቅሙን ሊያሳድግ እንደሚችል ሰፊ ትምህርት ሊሰጠው  ይገባል፡፡