ኮማንድ ፖስቱ 835 ህገ-ወጥ ታጣቂዎችን በተጨማሪ ያዘ

163

አሶሳ ጥር 8/2011 በቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና ኦሮሚያ ክልሎች አጎራባች አካባቢዎች ህገ-ወጥ የጦር መሣሪያ በመታጠቅ የህይወትና ንብረት ውድመት በማድረስ ወንጀል የተጠረጠሩ 835 ሰዎችን በተጨማሪ  መያዛቸው ተገለጸ፡፡

የሁለቱ ክልሎችን አጎራባች አካባቢዎች ሠላም ለመመለስ የተቋቋመው ኮማንድ ፖስት አባል፣  በሃገር መከላከያ ሠራዊት የምዕራብ ዕዝ ኢንዶክሪኔሽንና የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮሎኔል ጌትነት አዳነ ዛሬ ለኢዜአ እንደተናገሩት ኮማንድ ፖስቱ እንደቀድሞ ሁሉ ባለፈው ሳምንትም ውጤታማ ስራዎችን አከናውኗል፡፡

ባለፈው ሳምንት ብቻ ህገ-ወጥ የጦር መሣሪያ ታጥቀው የአካባቢውን ሠላም ሲያውኩ የነበሩ 835 ሰዎችን በተጠርጣሪነት መያዛቸውን አስረድተዋል፡፡

ከተያዙት ተጠርጣሪዎች መካከል  428 ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ካማሽ እና አሶሳ ዞን ማኦኮሞ ልዩ ወረዳ እና አሶሳ ከተማ አስተዳደር ውስጥ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡

ቀሪዎቹ ደግሞ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ፣ ምሥራቅ ፣ ሆሩ ጉድሩና ቄለም ወለጋ  እንዲሁም  ቡኖ በደሌ እና ኢሉአባቦር ዞኖች የተያዙ መሆናቸውን  ኮሎኔል ጌትነት አመልክተዋል፡፡

ግለሰቦቹ የታጠቋቸው 61 ክላሽንኮቨና  105 ዘመናዊ ያልሆኑ ጠመንጃዎች ፣ ስምንት ሽጎጦች፣ 17 የአድማ ብተና መሣሪያዎች፣ 1ሺህ 123 የክላሽንኮቭ፣ የሽጉጥ፣ የሞርታር እና ሌሎች ጥይቶት መያዛቸውንም  ገልጸዋል፡፡

እንዲሁም ዘጠኝ አይሱዙ የጭነት ተሽከርካሪዎች ፣ሁለት አምቡላንሶች፣ 5 ሚኒባሶች እና 26 ሞተር ብስክሌቶች እንደተያዙ አስረድተዋል፡፡

ከዚህ ሌላ ግለሰቦቹ ይገለገሉባቸው የነበሩ 19 ተንቀሳቃሽ የእጅ ስልኮች፣ የአምስት ሺህ 910 ብር ተንቀሳቃሽ የእጅ ስልኮች ቅድመ ክፍያ ካርዶች እና ኮምፒተሮች ከነፕሪንተራቸው ኮማድ ፖስቱ በቁጥጥር ስራ አውሏል፡፡

እንደ ኮረኔል ጌትነት ገለጻ የተያዙት የጦር መሣሪያዎች፣ ተሽከርካሪዎች እና ሌለችም ቁሳቁሶች የታጠቀው ኃይል ከመንግስት መዋቅርና ከህብረተሰቡ በመዝረፍ ለጥፋት ድርጊቱ የተጠቀማቸው ናቸው፡፡

ባለፈው ሳምንት በምዕራብ ወለጋ በሚገኙ የመንግስት እና የግል ባንኮች  ዝርፊያ እና በመንግስት ተቋማት ላይ የማቃጠል ጥፋት መፈጸሙን አመልክተዋል፡፡

ኮማድ ፖስቱ በአካባቢው በተፈጸመው ጥቃት በሰው ህይወት ላይ ጉዳት እንዳያደርስ ዋነኛ ትኩረት አድርጎ መስራቱን ያመለከቱት ኮረኔል ጌትነት በአሁኑ ወቅት ጥፋቱን የፈጸሙትን ለመያዝ የተጠናከረ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ችግሩ የተከሰተበት አካባቢ ለጉዞ አመቺ ባለመሆኑ በፍጥነት ወደ አካባቢው ለመድረስ ሠራዊቱ ሄሊኮፕተር መጠቀሙን ጠቅሰዋል፡፡

ሀኖም በማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን የተዘረፉ ባንኮች ቁጥር  ተጋኖ መቅረቡና አየር ኃይል አካባቢውን በሄልኮፕተር እንደተበደበ ተደርጎ በሃሰት እየተናፈሰ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

" ይህም የታጠቀው ኃይል ህብረተሰቡ ውስጥ በመመሸግ እና ህዝቡን በማስፈራራት የተጠናከረ አቅም ያለው ለማስመሰል የሚያደርገው ሩጫ ነው"ብለዋል ዳይሬክተሩ፡፡

የተያዙት ሰዎች  በአጭር ጊዜ ወደ ፍርድ ቤት ለማቅረብ የተደራጀ የፌደራል ጠቅላይ አቃቢ ህግ ቡድን ወደ አካባቢው መግባቱንም አስታውቀዋል፡፡

ኮማንድ ፖስቱ ባከናወናቸው ተግባራት የህብረተሰቡ እገዛ እየጨመረ መምጣቱን ገልጸው በተለይም ከባንክ ዘረፋ ጋር በተያያዘ ያለውን ትክክለኛ እውነታ ኮማንድ ፖስቱ በቅርቡ ለህዝብ ይፋ እንደሚያደርግ ኮረኔል ጌትነት አስታውቀዋል፡፡

ኮማድ ፖስቱ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና ኦሮሚያ ክልሎች አጎራባች አካባቢዎች በደረሰው ጥፋት የዛሬዎቹን ጨምሮ በአጠቃላይ 1ሺህ6 ሰዎችን እንዲሁም በርካታ የጦር መሣሪያ፣ ተሸከርካሪዎች እና ገንዘብ  ተይዟል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም