በቄለም ወለጋ ዞን ተዘግተው የነበሩ 79 ትምህርት ቤቶች ስራ ጀመሩ

1256

ነቀምት ጥር 8/2011 በቄለም ወለጋ ዞን ተከስቶ በነበረው የፀጥታ ችግር ተዘግተው የነበሩ 79 ትምህርት ቤቶች ስራ መጀመራቸውን የዞኑ ትምህርት ቤቶች  ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

የጽህፈት ቤቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ ተስፋ በሪሶ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለፁት  በዞኑ በነበረው ችግር አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ከ15 ቀናት በላይ የመማር ማስተማር ስራ አቋርጠው ቆይተዋል ።

የአካባቢውን የመረጋጋት ሁኔታ ተከትሎ ከህብረተሰቡ ጋር በተደረገ ውይይት ካለፈው ሳምንት ጀምሮ 79ኙ ትምህርት ቤቶች ስራ መጀመራቸውን ተናግረዋል።

“ወደ መደበኛ ሥራቸው ከተመለሱት ትምህርት ቤቶች መካከል 19ኙ በደምቢ ዶሎ ከተማና ቀሪዎቹ ወረዳዎች ውስጥ በገጠር የሚገኙ ናቸው” ብለዋል ።

ወደ መደበኛ ሥራ ያልገቡ ትምህርት ቤቶችን ሥራ ለማስጀመር ከኃይማኖት አባቶች፣አባ ገዳዎች፣ የሃገር ሽማግሌዎችና የወላጅ መምህራን ህብረት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ስራ አስኪያጁ አስታውቀዋል።

የቄለም መሰናዶ ትምህርት ቤት የወላጅ መምህራን ሕብረት ሊቀመንበር አቶ ብርሃኑ አጋ በሰጡት አስተያየት ተማሪዎች በማህበራዊ ድረ- ገፅ በመመራት በተደጋጋሚ ትምህርት ለማቋረጥ መገደዳቸውን ገልጸዋል።

በተለይ ችግሩ የ12ኛና የ10ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና በሚወስዱ ተማሪዎች ላይ ጫና እንዳያሳድር የባከነውን የትምህርት ክፍለ ጊዜ በቅዳሜና እሁድ ለማካካስ ከመምህራን ጋር ስምምነት ላይ መደረሱን ጠቁመዋል።

የባከኑ የትምህርት ክፍለ ጊዜያትን ለማካካስ ከቅዳሜና እሑድ በተጨማሪ ትምህርት ቤቶች ለዕረፍት በሚዘጉባቸውን ጊዜያት ትምህርት እንዲሰጥ ማህበሩ መወሰኑን የተናገሩት ደግሞ የቄለም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የመምህራን ማህበር ሊቀመንበር መምህር መልካሙ ቱጁባ ናቸው፡፡

በሰዮ ወረዳ የአለኩ መሰናዶ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ለሊሣ ዴቲ በበኩላቸው “ትምህርት ቤቱ ባለፈው ሰኞ በመከፈቱ 85 በመቶ የሚሆኑ ተማሪዎች በትምህርት ገበታ ላይ ናቸው ” ብለዋል ።

ተማሪዎቹን ወደ ትምህርት ቤት ለማምጣት በተደረገው እንቅስቃሴ የኃይማኖት ተቋማትና የእድሮች ሚና ከፍተኛ እንደነበር ርዕሰ መምህሩ አስታውቀዋል ።