ጥምቀትን በዓለም ቅርስነት የማስመዝገቡ ውጤት ቀጣይ ዓመት ይታወቃል

129

የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን የጥምቀት በዓልን በሰው ልጆች ወካይ የዓለም ቅርስነት የማስመዝገቡ ውጤት በመጪው ዓመት እንደሚታወቅ ገለጸ። 

በባለስልጣኑ የባህል ጥናት ተመራማሪ አቶ ገዛኸኝ ግርማ ለኢዜአ እንዳሉት የጥምቀት በዓልን በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ለማስመዝገብ ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ የተለያዩ ዝግጅቶች ተደርገዋል።

በአክሱም፣ በጎንደር፣ በላልይበላና በጃንሜዳ የጥምቀት በዓል አከባበርን የሚገልጹ የጽሑፍ፣ የፎቶግራፍ፣ የተንቀሳቃሽ ምስልና የድምጽ መረጃዎች ተደራጅተው ለገምጋሚ አካል መቅረባቸውንም ገልጸዋል።

የጥምቀት በዓልን በሰው ልጆች ወካይ ዓለም አቀፍ ቅርስነት የማስመዝገቡ ውጤት ህዳር 2012 ዓ.ም ይታወቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ አቶ ገዛኸኝ ተናግረዋል።

ባለስልጣኑ ጥምቀት በዓለም የማይዳሰሱ ቅርሶች መዝገብ እንዲመዘገብ አስፈላጊውን መረጃዎች ለዩኔስኮ መላኩን ነው ያነሱት።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን የውጭና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ኃላፊና የአዲስ አበባ አገረ ስብከት የቅዱስ ፓትሪያርኩ ረዳት ሊቀ-ጳጳስ ዶክተር አቡነ አረጋዊ እንዳሉት የጥምቀት በዓል ከኃይማኖታዊ ይዘቱ ባሻገር ለአገር ገጽታ ግንባታ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው።

የጥምቀት በዓል ለቱሪስት ፍሰት አስተዋጽኦ የሚያበረክት በመሆኑ ቤተ-ክርስቲያኗ በዓሉ የዓለም ቅርስ ሆኖ እንዲመዘገብ የበኩሏን ጥረት እያደረገች ነው ብለዋል።

ከዚህ በፊት ኢትዮጵያ የሲዳማን ዘመን መለወጫ ፍቼ ጫንበላላ፣ የገዳ ስርዓትና የመስቀል በዓልን በዩኔስኮ የማይዳሰስ የሰው ልጆች ወካይ ዓለም አቀፍ ቅርስ ሆነው እንዲመዘገቡ አድርጋለች። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም