ሀገራዊ ለውጡ እንዳይቀለበስ የድርሻውን እንደሚወጣ የድሬዳዋ ኢህአዴግ ወጣቶች ሊግ ገለጸ

126

ድሬዳዋ ጥር 8/2011 ሀገራዊ ለውጡ ሳይደናቀፍ ወደ ሚፈለገው ደረጃ እንዲደርስ የድርሻውን እንደሚወጣ የድሬዳዋ ኢህአዴግ ወጣቶች ሊግ አስታወቀ።

ሊጉ ነገ የሚጀምረውን አራተኛ መደበኛ ጉባኤ አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል ።

የሊጉ ሊቀመንበር ወጣት እስክንድር አህመድ እንደገለጸው  ሀገራዊ ለውጡን ዳር ለማድረስ ወጣቶች ህብረታቸውን ጠብቀው በተቀናጀ መንገድ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ለማስቻል እየተሰራ ነው፡፡

ወጣቶች   በብሔር ፣ በኃይማኖትና በጎሳ ሳይለያዩ ህብረታቸውን አጠናክረው ሀገራዊ ለውጡ እንዳይቀለበስ  ለማድረግ የድርሻቸውን እንደሚወጡም ተናግሯል፡፡

"ሀገራዊ ለውጡ እንዲመጣ ወጣቱ የህይወት መስዋዕትነት ከፍሏል፣ ለውጡ የኛ የወጣቶች ሀብት ነው፣ ከለውጡ ተጠቃሚ ለመሆን ሌት ተቀን እንሰራለን"ብሏል፡፡

የሊጉ አባላት በሁከትና ብጥብጥ ለውጡን ለማደናቀፍ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎችን በመለየት ለህግ በማቅረብ ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ አመላክቷል ።

"ሊጉ ነገ በሚጀምረውና ለሁለት ቀናት በሚቆየው አራተኛ መደበኛ ጉባኤ  ለውጡን በሚፈለገው አቅጣጫ ማራመድ የሚችሉ የአዳዲስ አመራሮች ምርጫ ይደረጋል" ሲል የሊጉ ሊቀመንበር ገልጿል።

ወጣቱ ሀገራዊ ለውጡን ለማስቀጠል ፣  የልማትና የሥራ ዕድል ተጠቃሚነታቸውን ማጎልበት በሚችልበት ዙሪያ ውይይት በማድረግ የአፈጻጸም አቅጣጫ እንደሚቀመጥ ይጠበቃል።

የድሬዳዋ ኢህአዴግ ወጣቶች ሊግ በገጠርና ከተማ 10 ሺህ 600 አባላት እንዳሉት  ተመልክቷል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም