አጀንዳ 2063 ለማሳካት የግዥና አቅርቦት ሰንሰለት ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ ነው

164

ሀዋሳ ጥር 8/2011 አፍሪካ ተፎካካሪ ፣ ሰላማዊና የበለጸገች አህጉር እንድትሆን ታስቦ የተቀረጸውን የ2063 አጀንዳ ለማሳካት የግዥና አቅርቦት ሰንሰለት ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ መሆኑን የአፍሪካ ሕብረት አስታወቀ፡፡

በግዥና አቅርቦት ሰንሰለት ላይ የሚያተኩር አውደ ጥናት በሀዋሳ ከተማ መካሄድ ጀምሯል፡፡

አውደ ጥናቱ ትናንት በሃዋሳ ከተማ ሲጀምር በአፍሪካ ህብረት የግዥ ዋና ኃላፊ ወይዘሮ ቴሬዛ ኔጉኪ እንዳሉት አፍሪካን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሳደግ የተያዘውን የ2063 አጀንዳ ስኬታማ ለማድረግ የግዥና የአቅርቦት ሰንሰለትን ማጤን ተገቢ ነው።

"በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ የግዥና አቅርቦት ሰንሰለት ኤክስፐርቶችን ማፍራት" የሚለው የአውደ ጥናቱ ዋና ዓላማ መሆኑን ገልጸዋል።

በሕብረቱ የግዥ፣ የጉዞና የንብረት ኮሚሽነር የሆኑት ወይዘሮ ካሪን ቱሬ በበኩላቸው በ2063 የበለጸገች፣ ሰላማዊ፣ መልካም አስተዳደር የሰፈነባት አፍሪካን እውን ለማድረግ ትኩረት መሰጠቱን አስታውቀዋል፡፡

ጠንካራ አህጉራዊ ማንነት ያለው ህዝብ ለመገንባትና በአለም አቀፍ ደረጃ ተጽእኖ ፈጣሪ አህጉር ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡

ከግዥ ጋር ተያይዞ የሚፈጠሩ የሙስናና የተንዛዛ የግዥ ስርዓት ችግርን ለመፍታት የምስራቅ አፍሪካና ደቡባዊ አፍሪካ አገሮች የጋራ ገባያ (ኮሜሳ)፣ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ) እና በሶማሊያ የአፍሪካ ሕብረት የሰላም አስከባሪ (አሚሶም)ን ጨምሮ  በህብረቱ ስር ባሉ ሌሎች ድርጅቶ ያለውን የግዥ ሂደት ቀልጣፋ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

የግዥና አቅርቦት ሰንሰለቱ በቀጣይ በአህጉሪቱ በሚገኙ አገራት ተግባራዊ እንደሚሆንና ከዚህ ጋር በተያያዘ የሚፈጠሩ ችግሮችን ለመፍታት እንደሚያስችል ገልጸዋል።

የአፍሪካ ሕብረት የ2063 አጀንዳዎችንና የህብረቱ ስትራቴጂክ እቅዶችን ወደ ምጣኔ ሀብታዊና ማህበራዊ ውጤቶች ለመቀየር የግዥና አቅርቦት ሰንሰለት ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ለአምስት ቀናት በሚቆየው አውደ ጥናት ከኮሜሳ ፣ ኢጋድ፣ አሚሶም፣ ሌሎች የአፍሪካ ሕብረት አካል የሆኑ ድርጅቶችና ሀገራት የተወከሉ የሎጅስቲክና የግዥ ከፍተኛ ባለሙያዎች በመሳተፍ ላይ ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም