በማይጨው ከተማ በጥምቀት በዓል የቱሪስት መዳረሻዎችን ለማስተዋወቅ እንደሚሰራ ተጠቆመ

367

ማይጨው ጥር 8/2011 በክልል ደረጃ በማይጨው ከተማ የሚከበረውን የጥምቀት በዓል ምክንያት በማድረግ የአካባቢውን የኢንቨስትመንትና የቱሪዝም መዳረሻዎችን ለማስተዋወቅ እንደሚሰራ የትግራይ ደቡባዊ ዞን መስተዳድር አስታወቀ፡፡

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪና የበዓል ዝግጅት አቢይ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ረዳኢ ሃለፎም ለኢዜአ እንደገለጹት ፣ የጥምቀት በዓልን በክልል ደረጃ በማይጨው ከተማ እንዲከበር ዝግጅት ሲደረግ ቆይቷል።

በጥምቀት በዓል ላይ በአካባቢው ፣ በአገር ውስጥና በውጪ የሚኖሩ የክልሉ ተወላጆች ተሳታፊ እንደሚሆኑም ተናግረዋል።

የጥምቀት በዓል አጋጣሚውን በመጠቀም የዞኑን የኢንቨስትመንት አማራጮችና የቱሪዝም መዳረሻዎችን ለማስተዋወቅም የዝግጀት ሥራው መጠናቀቁን አመልክተዋል።

ከበዓሉ ጎን ለጎን በዕቅድ ለሚከናወኑ ሥራዎችም ስምንት ኮሜቴዎች ተዋቅረው ወደ ተግባራዊ ሥራ መግባታቸውን ነው አቶ ረዳኢ የገለጹት።

የበዓሉን አጋጣሚ በመጠቀም የሐሸንጌ ሐይቅ እና የህጉም-ብርዳና የግራካህሱ የተፈጥሮ ደንን ጨምሮ በደቡባዊ ዞን ያለውን የግብርና ኢንቨስትመንት አማራጮችና አመቺነትን ለማስተዋወቅ የሚረዳ ፕሮግራም ተዘጋጅቷል።

ከእዚህ በተጨማሪ በዞኑ የሚገኙ የአባ ተክለሃይማኖትና የአባ ጉባ ገዳማት፣ በማይጨው የአባት አርበኞችና የጣሊያን ወታደሮች አጽም ያረፈበት ሙዚየም፣ የጥላሁን ይግዛው መቃብርና ሌሎች የቱሪስት መስህብ ስፍራዎችን ለማስተዋወቅ የጉብኝት ፕሮግራሞች ተዘጋጅተዋል፡፡

በማይጨው ከተማ ዙሪያ የሚገኙና ከጣሊያን ወራሪ ጦር ጋር ከፍተኛ ተጋድሎ የተካሄደባቸው የጽበትና ሌሎች ተራሮችም በበዓሉ እንግዶች ከሚጎበኙ ታሪካዊ ቦታዎች መካከል ይጠቀሳሉ።

“ማይጨው ከተማ ከየት ወዴት” በሚል ርዕስ የተዘጋጀና የከተማዋ ታሪካዊ አመጣጥ፣ እድገትና የኢንቨስትመንት አመቺነትን የሚዳስስ የፓናል ውይይት እንደሚደረግም ዋና አስተዳዳሪው አስታውቀዋል፡፡

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የትግራይ ደቡባዊ ዞን ሀገር ስብከት ጽህፈት ቤት ዋና ፀሐፊ ሊቀ ትጉሃን ረዳኢ ብርሃኑ በከተማው የጥምቀት በዓል ጥንታዊ ይዘቱን ሳይለቅ እንደሚከበር ተናግረዋል።

የጥምቀት በዓሉ ከሃይማኖታዊ ይዘቱ በተጨማሪ በክልሉ ተወላጆች መካከል የባህል ልውውጥን በማዳበር በህዝቦቹ መካከል ጠንካራ አንድነትን ለመፍጠር መልካም ዕድል እንደሚፈጥር አስታውቀዋል።

የማይጨው ከተማ ንግድ ዘርፍ ማህበራት አመራር አባል አቶ ገብረስላሴ ከበደ በሰጡት አስተያየት፣ የጥምቀት በዓልን ለማክበር የሚመጡ እንግዶችን በአግባቡ ለማስተናገድ የከተማው ንግድ ማህበረሰብ ዝግጅቱን አጠናቋል።

በበዓሉ ምክንያት በመኝታ አገልግሎት፣ በምግብና በመጠጥ ዋጋ ላይ ምንም አይነት ጭማሪ እንዳይረደግ ከንግዱ ማህበረሰብ አባላት ጋር በተደረገው  ውይይት ከስምምነት ላይ መደረሱን ነው አቶ ገብረስላሴ ያስታወቁት፡፡