ዓመታትን ለዘለቁ የህበረተሰቡ የልማት ጥያቄ ምላሽ መሰጠት ይገባል--- ቋሚ ኮሚቴው

59

ጎባ ጥር 7/2011 በባሌ ዞን ከለውጡ በፊትና በኋላም ሳይፈቱ የቀጠሉ የህብረተሰቡ የመንገድና የውሃ መሰረተ ልማት ጥያቄ ምላሽ ሊሰጣቸው እንደሚገባ የጨፌ ኦሮሚያ የሰው ሀብት ልማት ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ ፡፡

ቋሚ ኮሚቴው ሰሞኑን  በዞኑ ሶስት ወረዳዎች ላይ ያካሄደውን የመስክ ምልከታ የማጠቃለያ መድረክ  በባሌ ሮቤ ከተማ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የዞኑ የመንግስት ስራ ኃላፊዎች ጋር ተወያይቷል ፡፡

የዞኑ ማህበረሰብ ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ ቅሬታ ሲያቀርብባቸው የነበሩ የመንገድ፤ የውሃና ሌሎች የመሰረተ ልማት ጥያቄ  ዛሬም ድረስ ምላሽ ሳያገኙ መዝለቃቸው በመስክ ምልከታቸው ማረጋገጣቸውን ቋሚ ኮሚቴው ገልጿል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ተስፋዬ ገሾ እንደተናገሩት በዞኑ የሚገኙ ሮቤ፣ አጋርፋና ጎባ ወረዳዎችን ተዘዋውረው ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር ውይይት አድርጓል፡፡

በመስክ ምልከታውና ከህብረተሰቡ ጋር ባደረጉት ውይይት በዚሁ አካባቢ ግንባታቸው ተጀምረው መጠናቀቅ ከነበረባቸው ዓመታትን ያሰቆጠሩ የሚኦ -አሊ- አጋርፋ የመጠጥ ውሃ ፕሮጄክትና ከገጠር መንገድ መሰረተ ልማት  ጋር የተያያዙ ችግሮች አሁንም መፍትሄ ያላገኙ ቀጣይ የመንግስት የቤት ስራ መሆናቸውን አመልክቷል፡፡

ከወጣቶች ተዘዋዋሪ የብድር ገንዘብ ጋር ተያይዘው የሚነሱ ቅሬታዎች፣  በከተሞች አካባቢ የሚስተዋሉ ህገ ወጥ የመሬት ወረራ እየተበረከተ መምጣትና የህግ የበላይነት የማስከበሩ ጉዳይ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች መሆናቸውንም እንዲሁ፡፡

አቶ ተስፋዬ እንዳሉት ቋሚ ኮሚቴው የአካባቢው ማህበረሰብ ችግር መገምገም ብቻ ሳይሆን ችግሮቹ እንዲፈቱ ለተግባራዊነቱም በየደረጃው ከሚገኙ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ጋርም አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል እንደሚያደርጉም ገልጸዋል፡፡

ከአጋርፋ ወረዳ ነዋሪዎች መካከል አቶ ኡስማን ሁሴን እንዳሉት  የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቱ ግንባታ በ2002 ዓ.ም. የተጀመረ ነው ።

ግንባታው በሁለት ዓመታት ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ ቢጀመርም እስካሁን ባለማለቁ  ንጹህ መጠጥ ውሀ ፍለጋ  ከአካባቢያቸው ርቀው በየቀኑ እስከ አስር ኪሎ ሜትር ድረስ ለመጓዝ እንደሚገደዱ ለቋሚ ኮሚቴው አስረድተዋል፡፡

ይህም በኑሮቸው ላይ  ጫና እያሳደረባቸው በመሆኑ ጉዳዩ የሚመለከተው አካላት እልባት እንዲሰጡቸው ቋሚ ኮሚቴው ግፊት እንዲያደርጉላቸው የሚፈልጉ መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም