የተማረ የሰው ኃይል ለማፍራት ቤተ መጻህፍትን ማስፋፋት ይገባል ተባለ

120

ሽሬ እንዳስላሴ  ጥር 7/2011 ብቃትና ችሎታ ያለው የተማረ የሰው ኃይል ለማፍራት ቤተ መጻህፍትን ለማስፋፋት ትኩረት መስጠት እንደሚያስፈልግ የትግራይ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር ዶክተር ደብረጽዮን ገብረ ሚካኤል አስገነዘቡ።

የሽሬ ልማት ማህበር ከ20 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ በሽሬ እንዳስላሴ ከተማ ያስገነባው ዲጂታል ቤተ መጻህፍት ትናንት አገልግሎት ጀምሯል፡፡

በምረቃው ሥነ ሥርዓት ላይ ቀዳማዊት እመቤት ወይዘሮ ዝናሽ ታያቸው ተገኝተዋል።

ዶክተር ደብረጽዮን በሥነ ሥርዓቱ ላይ እንደተናገሩት  በዕውቀት ላይ የተመሰረተ ትውልድ ለመገንባትና ጥራት ላይ ያለው ትምህርት  ለመስጠት ደረጃቸውን የጠበቁ ቤተ መጻህፍትን መገንባት ወሳኝነት አለው።

በሙያቸው ተወዳድረው ብቃታቸውና ችሎታቸው የሚያስመስክሩ ወጣቶች ለማፍራትና ከዘመኑ ጋር ለመጓዝ ዲጂታል ቤተ መጻህፍትን መገንባት ቅድሚያ የሚሰጠው ሥራ መሆን እንደሚገባው አመልክተዋል፡፡

የሽሬ ልማት ማህበር በአገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ አባላቱና ደጋፊዎች በማስተባበር ለአገልግሎት ያበቃው ቤተ መጻህፍት ብቃት ያላቸው ተማሪዎችን ለማፍራት እንደሚያስችል ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ እምነታቸውን ገልጸዋል።

በከተማው ለሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት  ለመገንባት የመሠረት ድንጋይ ያኖሩት ቀዳማዊ እመቤት ወይዘሮ ዝናሽ ታያቸው ቤተ መጻህፍቱን ለማጠናከር አስተዋፅኦ እንደሚያደርጉ   እጠብቃለሁ ብለዋል።

ማህበሩም ቤተ መጻህፍቱን ለምረቃ በማብቃቱ ዶክተር ደብረጽዮን አመስግነዋል።

የሽሬ ልማት ማህበር ፕሬዚዳንት መምህር ሙስጠፋ ሰዒድ በበኩላቸው የቤተ መጻህፍቱ ሕንፃ የተገነባው የማህበሩ አባላትና ደጋፊዎች እንዲሁም መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና የልማት አጋሮች ባደረጉት አስተዋጽኦ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ቤተ መጻህፍቱ በአንድ ጊዜ ከ300 በላይ አንባቢዎች የማስተናገድ አቅም እንዳለው ተናግረዋል።

ለህፃናትና ለአካል ጉዳተኞች አገልግሎት የሚሰጥ የንባብ ክፍሎች ተዘጋጅተዋል ብለዋል።

ለቤተ መጻህፍቱ ህዋዊ ኩባንያ ከ16 ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው 200 ዘመናዊ ኮምፒዩተሮች ለግሷል።

ቤተ መጻህፍቱ ለአገልግሎት በመብቃቱ ወሰን የሌለው ደስታ እንደተሰማቸው ለኢዜአ አስተያየታቸውን የገለጹት መምህር በዛብህ በርኽ ናቸው።

ወይዘሮ ፎትየን አበራ የተባሉ የከተማው ነዋሪ በበኩላቸው ቤተ መጻህፍት ከፍተኛ ዕውቀት የሚገበየበት በመሆኑ ተማሪዎች ከፍተኛ ዕድል እንዳገኙ ሊቆጥሩ ይገባል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም