የአገሪቱን ሰላም ለማስጠበቅና ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ ፖሊስ የጎላ ሚና እንዳለው ተጠቆመ

69
አምቦ ግንቦት 18/2010 የሀገሪቱን ሰላም በማስጠበቅ ዘላቂ ልማትን ከማረጋገጥ አንጻር ፖሊስ የማይተካ ሚና እንዳለው የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ምክትል ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ጠይባ ሀሰን ገለጹ፡፡ የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሌጅ በምዕራብ ሸዋ ዞን ሰንቀሌ ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ለ26ኛ ጊዜ  ያሰለጠናቸውን 6ሺህ 494 ፖሊሶችን ዛሬ አስመርቋል፡፡ በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የክልሉ ምክትል ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ጠይባ በሀገሪቱም ሆነ በክልሉ በመከናወን ላይ የሚገኙ የልማት ሥራዎች ያለ ሰላም ከግብ ሊደርሱ አይችሉም፡፡ ለዚህም ፖሊስ ልማቱ እንዲረጋገጥና የህዝቡን ሰላም ለመጠበቅ ሚናው ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ " የዛሬዎቹ ተመራቂዎችም ወንጀልን አስቀድመው በመከላከል እና ከራሳችሁ በላይ የህዝብን ጥቅም በማስቀደም የተጣለባቸውን ህዝባዊና አገራዊ ኃላፊነት በብቃት ሊወጡ ይገባል" ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር መላኩ ፈንታ በእዚህ ወቅት እንዳሉት በክልሉ የህግ የበላይነት ተረጋግጦ እና የህዝቦች ሰላም ተጠብቆ ለማየት የፖሊስ ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ "ተመራቂዎችም ከራስ በላይ ለህዝብ ጥቅም መቆም እና ህዝብን በታማኝነት ማገልገል ይጠበቅባቸዋል" ብለዋል፡፡ የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሌጅም በቀጣይ ጊዜያት የፖሊስ ሳይንስ ትምህርትን በመጀመሪያ ዲግሪ ለመስጠት ዝግጅት ማጠናቀቁንም ጠቁመዋል፡፡ በኦሮሚያ ፖሊስ ኮሌጅ የመደበኛ እና ሙያ ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት የሰንቀሌ ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ኃላፊ ኮማንደር ገመቹ ጎሞሮ በበኩላቸው በዛሬው ዕለት ከተመረቁ የፖሊስ አባላት መካከል 787 ሴቶች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ተመራቂ የፖሊስ አባላትም ባለፉት ስድስት ወራት ለ883 ሰዓታት ያህል ማህበረሰብ ተኮር የፀጥታ፣ ፖሊሳዊ ስነ ምግባር፣ በህገ መንግስት ማስከበርና በሌሎችም የፖሊስ ሙያዎች ንድፍ በተግባር የተደገፈ ስልጠና መውሰዳቸውን ገልጸዋል። ሰልጣኞቹ በክልሉ የተለያዩ ወረዳዎችና ዞኖች የሚመደቡ መሆናቸውም ኮማንደሩ አመልክተዋል። ከተመራቂ ምልምል የፖሊስ አባላት መካከል ኮንስታብል ፍቅርተ ሹምዬ በሰጠችው አስተያየት በስልጠና ወቅት ያገኘችውን እውቀት ወደ ስራ በመተግበር ሁሉንም ዜጋ በእኩልነት ለማገልገል መዘጋጀትዋን ገልፃለች። " የፖሊስነት ሥራ ከራስ በላይ ለህዝብ መቆም እንደሆነ ሁሉ፣ ከሁሉም በላይ ለሕዝቡ ፍትህ መረጋገጥ በጽናት እሰራለሁ " ብላለች። ከስልጠና በፊት ስለ ፖሊስ የነበረውን አመለካከት ከስልጠናው በኋላ ሙሉ በሙሉ መቀየሩን የገለጸው ደግሞ ሌላው ተመራቂ ኮንስታብል አብዲሳ ጋዲሳ ነው ፡፡ በቀጣይም ከሥራ አጋሮቹና ከህዝቡ ጋር በመሆን ህግንና ሰላምን በማስከበር ኃላፊነቱን ለመወጣት ዝግጁ መሆኑ ተናግሯል። " የሰላም ማስከበር ኃላፊነት ለፖሊስ ብቻ የሚሰጥ አይደለም፤ በሙያችን በብቃት ማገልገል እንድንችል ህዝባችንም ከጎናችን ሊቆም ይገባል " ያለው ደግሞ ተመራቂ ኮንስታብል ኢትዮጵያ አፈታ ነው፡፡ በዛሬው ዕለት ለምረቃ ከበቁ ተመራቂዎች መካከል የትራፊክ ፖሊስ አባላት፣ የማረሚያ ቤት ፖሊሶች፣ ልዩ ኃይል እና አትሌቶች እንዳሉበት ታውቋል፡፡ በምረቃው ስነስርዓት የክልል፣ የዞንና የወረዳ አመራሮችና የተመራቂ ቤተሰቦች ተገኝተዋል፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም