የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ለአምባሳደር ቆንጂት ስነጊዮርጊስ እውቅና አበረከተላቸው

81

አዲስ አበባ ጥር 6/2011 የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ለአምባሳደር ቆንጂት ስነጊዮርጊስ እውቅና አበረከተላቸው።

አምባሳደር ቆንጂት ስነጊዮርጊስ አውቅና የተበረከተላቸው በዲፕሎማሲው መስክ  ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ አገራቸውን በማገልገላቸው መሆኑም ተጠቁሟል።

አምባሳደር ቆንጂት የውጭ ጉዳይ ሚንስቴርን በ1950ዎቹ በለጋ አድሜያቸው ተቀላቅለው ከዴስክ ኦፊሰርነት እስከ ከፍተኛ አመራርነት አገልግለዋል።

አምባሳደር ቆንጂት ከዮዲት እምሩ በመቀጠል በኢትዮጵያ ሁለተኛዋ ሴት አምባሳደርም ናቸው።

አምባሳደሯ በኦቶዋ፣ ካይሮ፣ ቴል አቪቭና ቬይና በሚገኙ የኢትዮጵያ ሚሲዮኖች ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ሆነው ያገለገሉ ሲሆን፤ በአፍሪካ ህብረትና በተባባሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽንም ቋሚ መልዕክተኛ በመሆን ሰርተዋል።

ከሰኔ 2009 እስከ መስከረም 2011ዓ.ም ደግሞ ኢጋድ በመራው የደቡብ ሱዳን የሰላም ስምምነት ላይም ልዩ አማካሪ ነበሩ።

አምባሳደር ቆንጂት የተበረከታላቸውን እውቅና አስመልክተው ባደረጉት ንግግር፤ እርሳቸው በውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ሲቀጠሩ ለሴቶች የነበረው ቦታና አሁን ሴቶች የተሰጣቸው ትኩረት ሰፊ ልዩነት እንዳለው ተናግረዋል።

በተለይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ለሴቶች የሰጡትን ትኩረት አመስግነዋል።

ዲፕሎማቶች እንደ ብረት ጠንክረው ለአገራቸው እድገት እንዲሰሩ የመከሩት አምባሳደሯ፤ እርሳቸው ለስኬት የበቁት ለስራቸው ባላቸው ፍቅር መሆኑንም ገልጸዋል።

አምባሳደር ቆንጂት ስነጊዮርጊስ ዛሬ ካገኙት እውቅና በተጨማሪም ከዚህ በፊት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት እንዳበረከተላቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም