በባሌ ዞን በግብርና ዘርፍ የተሰማሩ ወጣቶች ውጤታማ መሆናቸውን ተናገሩ

72

ጎባ ጥር 6/2011 በባሌ ዞን በማህበራት ተደራጅተው በግብርና ዘርፍ የተሰማሩ ወጣቶች ውጤታማ ሆነናል አሉ።

የዞኑ የስራ ዕድል ፈጠራና የከተሞች የምግብ ዋስትና ጽህፈት ቤት በበኩሉ በተያዘው በጀት ዓመት 49 ሺህ የሚሆኑ ወጣቶችን ወደ ሥራ ለማስገባት እየሰራ ነሁ ብሏል፡፡

ወጣቶቹ በተሰማራንበት የግብርና ስራ ውጤታማ እየሆን በመምጣታችን ያለብንን የመንግሥት ብድርም በወቅቱ እየከፈልን ነው ብለዋል፡፡

ከወረዳው ወጣቶች መካከል ''አብዲ ቦሩ'' በሚል ስያሜ በስንዴ ልማት ሥራ የተሰማራው ማህበር ኃላፊ ወጣት ደረጀ ንጋቱ እንደገለጸው ከአካባቢያቸው ወጣቶች ጋር በመሆን በ2009 ከኦሮሚያ ብድርና ቁጠባ ተቋም 350 ሺህ ብር ብድር ወስደው ሥራ መጀመራቸውን ተናግሯል፡፡

ወጣቱ እንደሚለው በቀበሌያቸው ከሚገኘው ትምሀርት ቤት 15 ሄክታር መሬት በመኮናተር በመኽር ወቅት ካለሙት ስንዴ 250 ኩንታል ምርት አግኝተዋል፡፡

ዘንድሮ በዚያው መሬት ላይ ምርጥ ዘርን ጨምሮ ሌሎች የተሻሻሉ የግብርና አሰራሮችን በመጠቀም ከአምና 300 ኩንታል ማምረታቸውን ተናግረዋል።

አምና ያመረቱት አንዱን ኩንታል ስንዴ በአንድ ሺህ ብር ሂሳብ መሸጣቸውን የተናገረው ኃላፊው፣ ዘንድሮ ምርቱም ሆነ የገበያውም ሁኔታ የተሻለ በመሆኑ ጥሩ ነገር እንጠብቃለን ብሏል፡፡

በተሰማራንበት ሥራ ውጤታማ እየሆንን በመምጣታችን ሌሎች የመነሻ ካፒታል እጥረት ያለባቸው ወጣቶችም የዕድሉ ተቋዳሽ እንዲሆኑ በማሰብ ከተበደርነው ገንዘብ ውስጥ በወቅቱ የሚጠበቅብንን ድርሻ በመክፈል ኃላፊነታችንን እየተወጣን እንገኛለን ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡

ሌላው የወረዳው የብድሩ ተጠቃሚ የከኒሳ ማህበር አስተባባሪ ወጣት ታመነ በላይ በበኩሉ 300 ሺህ ብር በመበደር ከ10 ጓደኞቹ ጋር  በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት መሰማራታቸውን ተናግሯል፡፡

ወጣቱ እንዳለው አምና በሁለት ሄክታር ማሳ ላይ ያለሙትን ካሮት፣ ሽንኩርትና ቀይ ሥር ለገበያ በማቅረብ 300 ሺህ ብር አግኝተዋል።

”የዘንድሮ የግብዓት አጠቃቀማመችንና የዝናብ ስርጪቱም የተስተካከለ በመሆኑ ከዓምና የተሻለ ነገር እናገኛለን ብለን እንጠብቃለን” ብሏል፡፡

ወጣቱ በተሰማራበት መስክ ከዚህ በተሻለ ሁኔታ ውጤታማ እንዲሆን መንግስት በአካባቢያችን ላይ ከሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና ሌሎች ድርጅቶች ጋር የገበያ ትስስር እንዲፈጥርልን እንፈልጋለን ሲል አክሏል።

በተመቻቸልን የስራ መስክ በመሰማራት ከቤተሰብ ጥገኝነት ከመለቃቃችን ባለፈ ለሌሎች ወጣቶችም ጊዜያዊ ሥራ በመፍጠራችን ደስተኞች ነን ሲል ወጣት እንዳለው ተናግሯል ።

የዞኑ የስራ እድል ፈጠራና የከተሞች የምግብ ዋስትና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጫልችሳ ዘውዴ እንደገለጹት በተያዘው የበጀት ዓመት 49ሺህ ወጣቶችን ወደ ሥራ ለማስገባት እየተሰራ ነው፡፡

ባለፉት ስድስት ወራት ከ20ሺህ የሚበልጡት ወጣቶች በቋሚና ጊዜያዊ  ሥራ አግኝተዋል፡፡

በተለያዩ ወረዳዎች  ከ117 የሚበልጡ ሼዶችን እየተገነቡ ሲሆን፣በማይገባቸው ሰዎች የተያዙ 54 ሼዶችን በማስለቀቅ ለወጣቶቹ እንዲተላለፉ መመሪያ ተሰጥቷል፡፡

ወደ ስራ የገቡ ወጣቶች ያሉባቸውን የመነሻ ካፒታል እጥረት ለመፍታት ደግሞ ባለፉተ ስድስት ወራት 14 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር ብድርና 861 ሄክታር መሬት በግብርና ሥራ ለተሰማሩ ወጣቶች መመቻቸቱንም ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

በዞኑ 18 ወረዳዎች ውስጥ የስራ እድል ተጠቃሚ የሆኑ ወጣቶች በዋነኝነት በግብርና፣ በዶሮ እርባታ፣ በእንጨትና ብረታ ብረት ሥራ፣ በእንሰሳት ንግድና ማድለብ ዘርፎች ተሰማርተዋል፡፡

በባሌ ዞን ከ2009 ጀምሮ መንግስት ባመቻቸው ብድር ከ110 ሚሊዮን ብር በላይ ብድር ለተደራጁ ወጣቶች የተሰራጨ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ

ሰባት ሚሊዮን ብር  መመለሱን  ከጽህፈት ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም