የስንዴ ሰብላችን በኮምባይነር መሰብሰባችን ብክነትን አስቀርቶልናል— አርሶ አደሮች

253

ባህርዳር ጥር 6/2011 የደረሰ ሰብል በኮምባይነር በመሰብሰባቸው ጉልበት፣ጊዜ፣ ወጪና የምርት ብክነትን መቀነስ ያስቻላቸው መሆኑን አስተያየታቸውን የሰጡ የምዕራብና ምስራቅ ጎጃም አርሶ አደሮች ገለጹ ።

በአማራ ክልል በመኽር ወቅት  ከለማው መሬት ከ900 ሺህ ኩንታል በላይ የስንዴ ምርት በኮምባይነር መሰብሰቡ ተመልክቷል።

በምዕራብ ጎጃም ዞን ወንበርማ ወረዳ የዋዝንክስ ቀበሌ አርሶ አደር አምሳሉ ቆለጭ ለኢዜአ እንዳሉት  በመኽር ወቅት በሁለት ሄክታር ኩታገጠም ማሳ ያባዙትን የስንዴ ዘር በኮምባይነር አጭደው በመውቃት 60 ኩንታል ምርት አግኝተዋል ።

ከሰበሰቡት ምርት ውስጥ 45 ኩንታሉን ለአማራ ምርጥ ዘር ኢንተርፕራይዝ አቅርበው ኩንታሉን  1 ሺህ 580 ብር መሸጣቸውን ተናግረዋል ።

ከዚህ ቀደም የደረሰ ሰብል ከአጨዳ እስከ ውቂያ በሰው ጉልበት ለመሰብሰብ ለቀን ሰራተኛ ከፍተኛ ወጪ እንደነበረባቸው ያስታወሱት አርሶ አደሩ ዘንድሮ በኮምባይበር በመሰብሰባቸው ወጪያቸውን በግማሽ መቀነሳቸውን ተናግረዋል ።

“ያጋጥም የነበረውን እስከ ሶስት ኩንታል የምርት ብክነት አስቀርቶልኛል” ብለዋል ።

በወረዳው የማር ወለድ ቀበሌ  አርሶ አደር ዳኛቸው በቀለ በበኩላቸው በሩብ ሄክታር መሬት ያለሙትን የስንዴ ሰብል በኮምባይነር መሰብሰባቸውን ተናግረዋል ።

“ዘንድሮ ሰብሉን ከብክነትና ከእርጥበት በጸዳ መልኩ በመሰብሰቤ ያገኘሁት 10 ኩንታል ምርት ከዚህ ቀደም በጉልበት ከሚሰበሰው በመጠንም በጥራትም የተሻለ ነው” ብለዋል ።

ሰብልን በኮምባይነር በመሰብሰባቸው ጊዜና ጉልበት እንደቆጠበላቸው  የተናገሩት  ደግሞ በምስራቅ ጎጃም ዞን ደብረ ኤልያስ ወረዳ የጠጠር ጥጃ ጎጥ ቀበሌ  አርሶ አደር አተረፍ አንዷለም ናቸው።

“ሌሎች የአካባቢው አርሶ አደሮችም ሰብላቸውን በኮምባይነር ለመሰብሰብ ፍላጎት ቢኖራቸውም እጥረት እያጋጠመ በመሆኑ መንግስት አቅርቦቱን ሊያሻሽል ይገባል” ብለዋል ።

በክልሉ ግብርና ቢሮ የሰብል ልማት ዳይሬክተር አቶ አለባቸው አሊጋዝ  በመኽር ወቅት በ20ሺህ ሄክታር ኩታ ገጠም ማሳ የለማ የስንዴ ሰብል በኮምባይነር ታጭዶ መሰብሰቡን ተናግረዋል።

ዳይሬክተሩ እንዳሉት ከሰሜን ሸዋ፣ አዊ፣ ምዕራብና ምስራቅ ጎጃም ዞኖች 19ሺህ ከሚሆኑ አርሶ አደሮች ማሳ ላይ ሰብሉ ተሰብስቧል፡፡

“ሰብሉ የተሰበሰበው በ42 ኮምባይነሮችና በ64 አነስተኛ የእጅ መውቂያ መሳሪያዎች በመታገዝ  ነው” ብለዋል።

ከተሰበሰበው የስንዴ ሰብል ከ900 ሺህ ኩንታል በላይ ጥራቱን የጠበቀ ምርት መገኘቱን አመልክተዋል።

የኮምባይነር አቅርቦት እጥረት ችግር ለመፍታት ህብረት ስራ ማህበራት፣ ዩኒየኖችና ባለሃብቶች ከልማት ባንክ የገንዘብ ብድር አግኝተው ግዥ የሚፈፅሙበት ሁኔታ  እየተመቻቸ መሆኑን ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል ።

በክልሉ በ2009/2010 ምርት ዘመን ከ14 ሺህ ሄክታር በላይ ኩታ ገጠም ማሳ ላይ የስንዴ ሰብል በኮምባይነር ታጭዶ መሰብሰቡ ከክልሉ ግብርና ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።