በመቀሌ የአምስት ኪሎ ሜትር የእግር ጉዞ ተካሄደ

90

መቐለ ጥር 5/2011 በመቀሌ ከተማ "ስፖርትን በመስራት ከማይተላለፉ በሽታዎች ራሳችንን እንከላከል!" በሚል መሪ ቃል ዛሬ የአምስት ኪሎሜትር የእግር ጉዞ ተካሄደ።

የእግር ጉዞው አንድ ሰው በቀን በአማካይ 30 ደቂቃዎችን የእግር ጉዞ በማድረግ ከማይተላለፉ በሽታዎች ራሱን መከላከል እንደሚችል ግንዛቤ ለመስጠት ዓላማ ያደረገ መሆኑ ተገልጿል፡፡

የእግር ጉዞውን ያስጀመሩት የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሐጎስ ጎደፋይ ኢትዮጵያ ውስጥ 52 በመቶ የሚሆኑ ሰዎች ከስምንት በላይ በሚሆኑ የማይተላለፉ  በሽታዎች በየዓመቱ ለሞት እንደሚዳረጉ ገልጸዋል።

ለሞት አደጋ ከሚጋለጡ የኅብረተሰብ ክፍሎች መካከልም 51 በመቶ ያህሉ ከ40 ዓመት ዕድሜ በታች የሆኑ አምራች ዜጎች መሆናቸውን ኃላፊው ተናግረዋል።

ኅብረተሰቡ የአካል እንቅስቃሴ በማድረግ በሽታዎችን በቀላሉ መከላከል እንደሚችል ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

የትግራይ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ገነት አረፈ በበኩላቸው አገር የሚረከብ ጤነኛና አምራች ዜጋን ለመፍጠር ስፖርት ወሳኝ ሚና እንዳለው ገልጸዋል፡፡

በየደረጃው የሚገኙ አመራሮችና የስፖርት ባለሙያዎች ዓርአያ ሆነው ሊንቀሳቀሱ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ከእግር ጉዞው ተሳታፊዎች መካከል ወጣት ሰላም ልዑል ስፖርት የተስተካከለ የሰውነት ቁመና እንዲኖርና ጤነኛና ደስተኛ ለመሆን እንደሚያስችል ተናግራለች፡፡

አቶ አሰፋ ተሻገር በበኩላቸው የማይተለላፉ በሽታዎች እየጨመሩ በመምጣታቸው በባለሙያ የሚሰጥን ምክረ ሃሳብ በመጠቀም መከላከል እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

በእግር ጉዞው ላይ  በሺህዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ተሳትፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም