ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደቱን ለማስቀጠል የድርሻችንን እንወጣለን -የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች

94

ጋምቤላ ጥር 5/2011በጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ያለውን ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት ለማስቀጠል የድርሻቸውን እንደሚወጡ የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች አስታወቁ፡፡

ተማሪዎቹ በሰላም ዙሪያ ከሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ አቶ ኡባንግ ሜቶ ጋር ትናንት በጋምቤላ ከተማ ውይይት አድርገዋል፡፡

በውይይቱ ላይ የተገኙ አንዳንድ የዩኒቨርስቲው ተማሪዎች ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ያለውን ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት ለማስቀጠል እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡

ተማሪ ወደ ዩኒቨርሲቲው የሚገባው አስፈላጊውን ዕውቀት በመቅስም ለራሱም ሆነ ለአገሩ የተሻለ ዕድል ለመፍጠር ነው ያሉት ተማሪዎቹ ፣ ድብቅ ዓላማቸውን ለማስፈጸም ለሚሯሯጡ አካላት መሳሪያ ለመሆን መንቀሳቀስ እንደሌለባቸው አሳስበዋል፡፡

ብሔርን መሰረት ያደረጉ ግጭቶች በዩኒቨርሲቲው እንዳይከሰቱም ከትምህርታቸው ጎን ለጎን በሰላም ዙሪያ  እንደሚወያዩ  አስታውቀዋል፡፡

ከጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መካከል አንዱ ተማሪ ደረጀ ዳባ ዩኒቨርሲቲው ከተለያዩ አካባቢዎች የመጡ ተማሪዎች ከዕውቀት ባሻገር ቋንቋና ባህል የሚለዋወጡበት ቦታ መሆኑን ተናግሯል፡፡

"በተማሪዎች መካከል ያለው ግንኙነት በእርስ በእርስ መግባባት ላይ የተመሰረተና ሰላማዊ  ነው" ያለው ተማሪው፣ የዩኒቨርሲቲውን ሰላም በማስቀጠል የመማር ማስተማሩን ሂደት ለመደገፍ ድርሻቸውን እንደሚወጡ አመልክቷል፡፡

ተማሪ ፀሐይ ዘውዴ በበኩሏ በዩኒቨርሲቲው ውስጥ የሚነሱ የመልካም አስተዳደር ችግሮችንና አልፎ አልፎ የሚከሰቱ አለመግባባቶችን በውይይት እየፈቱ መሆኑን ገልጻለች፡፡

ችግሮችን በውይይት የመፍታቱ ሂደት የመማር ማስተማር ሂደቱን ሰላማዊ ከማድረጉም ባሻገር ተማሪው ለትምህርቱ ትኩረት እንዲሰጥ እንደሚያግዝ ተናግራለች፡፡

በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ያለው የመማር ማስተማር ሂደት ሰላማዊ በመሆኑ ትምህርቱን በአግባቡ እየተከታተለ መሆኑን የገለጸው ደግሞ ተማሪ አዶላ ክፍሌ ነው፡፡

ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደቱ እንዲቀጥል የድርሻውን እንደሚወጣ ተናግሯል፡፡

በውይይቱ ላይ የተገኙት የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ አቶ ኡባንግ ሜቶ እንደገለጹት ኢትዮጵያ አንድነቷን አስጠብቃ እንድትቀጥል የአገር ፍቅር ያለውና ኃላፊነት የሚሰማው ዜጋ መፍጠር ያስፈልጋል፡፡

ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ጋር የውይይት መድረኮችን በመፍጠር በቅርበት መነጋገሩ ለችግሮች  መፍትሄ ለማምጣት እንደሚያስችል ተናግረዋል፡፡

በተለይም ወጣቶች ነገ አገር ተረካቢ እንደመሆናቸው መጠን አንድነታቸውን በማጠናከር ለአገሪቱ ሰላምና እድገት እንዲተጉ አሳስበዋል፡፡

በውይይቱ መድረኩ ላይ ተማሪዎችን ጨምሮ የዩኒቨርሲቲው መምህራን፣የአስተዳደር ሰራተኞችና ጉዳዩ የሚመለከታው አካላት ተገኝተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም