በጅማ ሙዚየም ለሚገኙ ቅርሶች ተገቢ ጥበቃ እንዲደረግላቸው ተጠየቀ

965

ጅማ ጥር 4/2011 የጥንታዊ ስልጣኔ መገለጫ ለሆኑ ቅርሶች ተገቢውን ጥበቃና እንክብካቤ እንዲደረግላቸው የጅማ ከተማ ሙዚየም ጎብኚዎች ጠየቁ፡፡

ከጎብኚዎቹ መካከል የገና በዓልን ከእህቱ ጋር ለማሳለፍ ከቴፒ ከተማ የመጣው ወጣት ሙራድ ዳውድ  ጅማ ሙዚየም ውስጥ ከሚገኙ ቅርሶች በርካታ ታሪክንና ጥንታዊ የስልጣኔን ደረጃን  ለማወቅና ለመገንዝብ መቻሉን ለኢዜአ በሰጠው አስተያየት ገልጿል፡፡

“በሙዚሙ የሚገኙ ቅርሶች በጥበቃና እንክብካቤ ጉድለት አንዴ ከጠፉ መልሶ ለመተካት የማይቻል በመሆኑ በጥንቃቄ ሊያዙ ይገባል” ብሏል፡፡

የሚደረግላቸው ጥበቃ ሳይንሳዊ መንገድን የተከተለና አስፈላጊውን ግብአት በማሟላት  መሆን እንደሚገባም ጠቁሟል፡፡

በጅማ ሙዚየም ውስጥ የሚገኙ ቅርሶች የአካባቢውን ባህል፣ወግ፣ታሪክና የጥንታዊ ስልጣኔ ብቻን ሳይሆን አገራዊ የሆኑ ጥንታዊ መረጃዎችን ለትውልድ  የሚያስተምሩ በመሆኑ በሚመለከት አካል ተገቢ ጥበቃ እንዲደግላቸው ጠይቋል፡፡

ከአማራ ክልል የመጣው የጅማ ዩኒቨርስቲ ተማሪ የሆነው  አበበ አየነው  በበኩሉ የገና በዓልን ምክንያት በማድረግ የጅማ ሙዚየምን በመጎብኘቱ መደሰቱን ተናግሯል፡፡

ተማሪው እንዳለው በጅማ ሙዚየም በርካታ አይነት የጥንታዊ ስልጣኔ ማሳያ ቅርሶችን ይገኛሉ፡፡

የንጉሳዊያን አልባሳት፣ ጥንታዊ ጌጣጌጦች፣ ስጦታዎች፣ የጦር መሳሪያዎች፣ የእርሻ መሳሪያዎች፣ የዱር አራዊት ቅሪቶች፣ መመገቢያ ቁሳቁሶች፣ የዕደጥበብ ስራዎችን  ተማሪ አበበ ከጎበኛቸው መካከል እንደሆኑ አመልክቷል።

“ነገር ግን ቅርሶቹ  በጠባብ ክፍል ውስጥ ከመገኘታቸውም በላይ በቂ ብርሃን የሌላቸው በመሆኑ ለማስታወሻ  ያህል እንኳን ፎቶ ግራፍ ለመነሳት ምቹ አይደሉም” ብሏል፡፡

ያረጁና ጥገና የሚያስፈልጋቸው ቅርሶችም በሙዚየሙ ውስጥ ተቀምጠው ማየቱን ጠቁሟል፡፡

እነዚህ የጥናታዊ ስልጣኔ መገለጫ ቅርሶች በተገቢው ሁኔታ መያዝ የሚገባቸው በመሆኑ የሚመለከተው አካላት ትኩረት እንዲሰጠው ጠይቋል፡፡

የጅማ ከተማ ሙዚየም ኃላፊ አቶ ነጀቢ ራያ በሙዚየም ውስጥ ከ1ሺህ 500 የሚበልጡ ቅርሶች እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡

ከቅርሶች ብዛትና ባህሪ አንጻር ሙዚየሙ በቂ ክፍሎች እንደሌሉት አመልክተው በሙዚየም ውስጥ ከሚገኙ ቅርሶች መካከል ያረጁትን በመለየት  እየተጠገኑ አገልግሎት እንዲሰጡ እየተደረገ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

“በቀጣይ ቅርሶችን በተሻለ ሁኔታ ለመጠበቅ ሁለት ሙዚየሞችን መገንባት አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበት ጥናት እየተደረገ ነው” ብለዋል ፡፡

በጅማ ሙዚየም የሚገኙ ቅርሶችን በአማካኝ በዓመት እስከ 10 ሺህ የሚደርሱ የሀገር ውስጥና እስከ 3 መቶ በሚደረሱ የውጭ ጎብኚዎች  እንደሚታይ ኃላፊው አመልክተዋል፡፡