በፖሊስ የደንብ ልብስ ወንጀል የፈፀሙ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ

1117

አዲስ አበባ ጥር 4/2011 የፖሊስን የደንብ ልብስ በመልበስ ወንጀል የሚፈፅሙ ግለሰቦች መኖራቸውን እንደደረሰበትና ከፈፃሚዎቹ ጥቂቶቹን በቁጥጥር ስር ማዋሉን የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ገለጸ።

በዚህ ወር የሚካሄደው የጥምቀት በዓልና የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ስብሰባ ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲጠናቀቅ ዝግጅት ማድረጉንም ኮሚሽኑ አስታውቋል።

የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄነራል እንዳሻው ጣሰው ለኢዜአ እንደገለጹት በተለያዩ አካባቢዎች የፖሊስን የደንብ ልብስ በመልበስ ወንጀል የሚፈፅሙ ግለሰቦች መኖራቸው ተደርሶበታል፤ጥቂቶቹም በቁጥጥር ስር ውለዋል።

የወንጀሉ ፈፃሚዎች የፖሊስን የደንብ ልብስ በተለያየ መንገድ በእጃቸው እንደሚያስገቡ የጠቆሙት ኮሚሽነር ጄነራል እንዳሻው የወንጀሉ ተሳታፊዎችን በማጋለጥ በኩል ሕብረተሰቡ የተለመደ ትብብሩን እንዲያደርግም ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ሰራዊት ዩንፎርም ጋር ተመሳሳይነት ካላቸው የጎረቤት አገራትም የደንብ ልብሱ ለወንጀል መፈፀሚያነት ወደ አገር ውስጥ ሊገባ እንደሚችልም ጠቁመዋል።

በፖሊስ ሰራዊት ውስጥ እየሰሩ ያሉ ጥቂት ግለሰቦችም በወንጀል ድርጊቱ ተሳታፊ ሆነው በመገኘታቸው በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን ኮሚሽነሩ ገልፀዋል።

በተመሳሳይ ወንጀል የሚጠረጠሩ ግለሰቦችን በማጋለጥና ለፖሊስ ጥቆማ በመስጠት ህብረተሰቡ የተለመደ ትብብሩን እንዲያደርግም ኮሚሽነሩ ጠይቀዋል።

ፖሊስበተያዘው ወር ለሚካሔዱት የጥምቀት በዓልና የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ስብሰባም ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲጠናቀቅ ዝግጅት ማድረጉን ገልፀዋል።

ለዚህም ስኬት ህብረተሰቡ የተለመደ ትብብሩንና እንግዳ ተቀባይነቱን እንዲያሳይ በማለት ኮሚሽነሩ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።