የአፍሪካ አገሮች ዲፕሎማቶችና የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽነሮች በእንጦጦና ሱሉልታ ጉብኝት አደረጉ

1629

አዲስ አበባ ጥር 4/2011 የኢትዮጵያን የባህል ቀን ምክንያት በማድረግ መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ያደረጉ የአፍሪካ አገሮች ዲፕሎማቶችና የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽነሮች በእንጦጦና ሱሉልታ ጉብኝት አደረጉ።

ዲፕሎማቶቹ እንጦጦ የሚገኘውን የአፄ ሚኒልክ ቤተ መንግስት፣ በዚሁ አቅራቢያ የሚገኘውን የሚኒሊክና የእቴጌ ጣይቱ መታሰቢያ ሙዚየም እንዲሁም ሱሉልታ የሚገኘውን ሃይሌ ሙዚዬም ጎብኝተዋል።

የኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ በጉብኝቱ ወቅት እንዳሉት፤ ከተለያዩ የዓለም አገራት ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ እንግዶች እንደ ሁለተኛ ቤታቸው እንዲሰማቸው ማድረግ ያስፈልጋል።

ለዚህ ደግሞ ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ቅርሶች ለዓለም ለማስተዋወቅ በየጊዜው የኢትዮጵያ የባህል ቀን የጉብኝት መርሃ ግብር ይዘጋጃል ብለዋል።

ኢትዮጵያ የበርካታ የቱሪስት መስህቦች መገኛ መሆኗን የገለጹት ዶክተር ወርቅነህ “ለዲፕሎማቶቹና ለህብረቱ ኮሚሽነሮች የዛሬው ጉብኝት የመጀመሪያ እንጂ የመጨረሻ አይደለም” ብለዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ አቶ ነብያት ጌታቸው በበኩላቸው ኢትዮጵያ ከሌሎች አገሮች ጋር ያላት የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካና ማህበራዊ ትስስር ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የተከናወነው “የኢትዮጵያ የባህል ቀን” መርሃ ግብርም ለዚህ አንዱ ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።

በዛሬው ጉብኝት ተሳታፊ ከሆኑት መካከል በኢትዮጵያ የኮቲዲቮር አምባሳደር ኮፊ ያፒ “የአፍሪካ የነጻነት አርማ የጥቁሮች መመኪያ የሆኑትን የዳግማዊ አፄ ሚኒልክ ቤተ መንግስት በመጎብኘቴ በጣም ተደስቻለሁ” ብለዋል።

የአፍሪካ መመኪያ የሆነችው ኢትዮጵያ ሰፊ የቱሪስት መዳረሻ እንዲሁም አኩሪ ታሪክ ያላት ታላቅ አገር መሆኗን የሚያሳዩ ቦታዎች እንዳሏትም ተረድቻለሁ ብለዋል።