የአየርላንድ መንግስት ለኢትዮጵያ እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል---ጠቅላይ ሚኒስትር ሊዮ ቫራድካር

128

ሽሬ ጥር 4/5/2011 የአየርላንድ መንግስት ኢትዮጵያ ለምታካሂዳቸው የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማቶች ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስቴር አስታወቁ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ሊዮ ቫራድካር በትግራይ ሰሜናዊ ምዕራብ ዞን የእንዳባጉና የማይ ዓይኒ የኤርትራ ስድተኞች  መጠለያ ጣቢያዎችን ትላንት ጎብኝተዋል ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት እንደገለፁት መንግስታቸው ኢትዮጵያ በባህል፣ በቱሪዝም፣ በገጠር ሥራ እድል ፈጠራና በአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት እያኬሄደች ላለችው ሰራዎች የገንዘብና የቴክኒክ ድጋፉን አጠናክሮ ይቀጥላል።

በተለይ ኢትዮጵያ የህዝቧን  ኑሮ ለመለውጥ እያካሄደች ላለችው የምግብ ዋስትና መርሀግብር ቀጣይነት መንግስታቸው ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል ።

"በማህበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ግንባታ እየተደረገ ያለው ድጋፍ ይቀጥላል " ብለዋል ።

ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ኤርትራዊያን ስድተኞች ያለባቸውን ማህበራዊ ችግሮች ለማቃለል መንግስታቸው በተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ኮሚሽን በኩል ድጋፍ እንደሚደረግ ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ በተዘዋወሩባቸው አካባቢዎች በተደረገላቸው አቀባበል ደስተኛ መሆናቸውንም ገልፀዋል።

በምከትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕርግ የትግራይ ንግድ ኢንዱስትሪና ከተማ ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር አብራሃም ተከስተ በክልሉ ብሎም በሀገሪቱ የሚካሄዱ የልማት ሥራዎች  በራስ አቅም ቢሆኑም የአየርላንድ መንግስት ድጋፍ የራሱን አስተዋጻ እንዳለው ተናግረዋል ።

"የአየርላንድ መንግስት በግብርና፣  በትምህርት፣ በጤናና በምግብ ዋስትና መርሀ ግብር ለሚካሄዱ ሰራዎች ድጋፍ እያደረገ ነው" ብለዋል ።

ጠቅላይ ሚንስትሩ ቀደም ሲል  የደብረ ሮሃ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስትያናትን ጎብኝተዋል፡፡

በዚህ ወቅት እንደ ላሊበላ ዓይነት ዓለም አቀፍ ጎብኚዎች መዳረሻ የሆኑ ቅርሶችን ለምጣኔ ኃብታዊ ዕድገት፣ ለገጠር ቱሪዝምና የስራ እድል ፈጠራ ማዋል እንዲቻል የአየርላንድ መንግስት በትብብር እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

የአየርላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ሊኦ ቫራድካር በኢትዮጵያ የሶስት ቀናት የሥራ ጉብኝት ለማድረግ ባለፈው ማክሰኞ ነው አዲስ አበባ የገቡት።

ኢትዮጵያ እና አየርላንድ ረዥም ዘመን ያስቆጠረ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ያላቸው ሲሆን፤ እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር በ2014 የአየርላንድ ፕሬዝዳንት ሚካኤል ሄገንስ ኢትዮጵያን ጎበኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም