የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ሰራተኞች ነፃ የስራ ዘመቻ አከናወኑ

1226

አገልግሎት ጥር 4/2011 የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ሰራተኞች በዛሬው እለት 3ኛ ዙር የነፃ አገልግሎት የስራ ዘመቻ አከናወኑ።

በነፃ አገልግሎቱ እየተነካኩ ችግር የሚፈጥሩ የኤሌክትሪክ መስመሮችን የማለያየት፣ ያዘመሙ ፖሎችን የማቅናት እንዲሁም ሌሎች በመደበኛነት የሚሰሩ ተግባራትን ማከናወን ተችሏል።

የዘመቻ ስራው በመደበኛው የስራ ሰዓት ያልተጠናቀቁ ጅምር ስራዎችን ለማጠናቀቅ እንዲሁም በእለቱ የሚያግጥሙ የሃይል መቆራረጥ ችግሮችን በመጠገን አፋጣኝ ምላሽ መስጠት የሚያስችል መሆኑንም የአገልግሎቱ ኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ መላኩ ታዬ ገልፀዋለ።

በመርሃ ግብሩ ከዋና መስሪያ ቤትና ከሁሉም የክልሎች እንዲሁም የከተማ አስተዳድር የተውጣጡ ከ17 ሺህ በላይ ቋሚና ኮንትራት ሠራተኞች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ሰራተኞች ባለፈው ጥቅምት 03 እና 10 ቀን 2011 ዓ.ም በሁለት ዙር ባካሄዱት የነፃ አገልግሎት ከ3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት አገልግሎት መስጠት መቻሉን ዳይሬክተሩ አስታውሰዋል።

አራተኛው ዙር ተመሳሳይ ዘመቻ ጥር 18 ቀን 2011 ዓ.ም እንደሚካሄድም ለማወቅ ተችሏል።