በውላቸው መሰረት ያላጠናቀቁ የሥራ ተቋራጮች በከተማዋ በሚደረጉ ግንባታዎች ላይ እንዳይሳተፉ ሊደረግ ነው

538

አዲስ አበባ  ጥር 4/2011 በአዲስ አበባ ከተማ በመንግስት በጀት የሚሰሩ ፕሮጀክቶችን በውላቸው መሰረት ያላጠናቀቁ የሥራ ተቋራጮች ውላቸው ተቋርጦ  በማንኛውም የከተማዋ  ግንባታ እንዳይሳተፉ ሊደረግ መሆኑን ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ ገለፁ።

የከተማ አስተዳደሩ ዋና ኦዲተር ፕሮጀክቶቹን ከሚያሰሩት የከተማዋ መንግስት መስሪያ ቤቶች ጋር በሚቀጥሉት ሶስት ሳምንታት ውስጥ የፕሮጀክቶቹን አጠቃላይ አፈፃፀም ለከተማዋ የኮንስትራክሽን ቢሮ እንዲያቀርብ ምክትል ከንቲባው ትዕዛዝ አስተላልፈዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፕሮጀክቶችን ከሚሰሩ ሥራ ተቋራጮች ጋር በግንባታ መጓተት ዙሪያ በተጠራው ስብሰባ የፕሮጀክቶቹ አፈፃፀም ሪፖርት የቀረበ ሲሆን ብዙዎቹ በውላቸው መሰረት እየሄዱ አይደለም።

በኢሌሌ ሆቴል በተደረገው ስብሰባ ላይ የከተማዋ ምክትል ከንቲባ በመንግስት በጀት የሚሰሩ ፕሮጀክቶች መጓተት በተመለከተ ጉዳዩ በተደጋጋሚ ሲነሳ የነበረና መፍትሄ ያላገኘ መሆኑን አስታውሰዋል።

እስካሁን በዘርፉ በሚካሄዱ ውይይቶች ከይዞታ ጋር የተያያዘ፣ ከውጭ ምንዛሬ ጋር የተያያዘና መሰል ተመሳሳይ ምክንያቶች ሲቀርቡ መቆየታቸውንና ብዙዎቹ ግን ከችግሩ ጋር የሚያያዙ ባለመሆናቸው ከዚህ በኋላ ተቀባይነት የላቸውም ሲሉ ገልፀዋል።

ምክንያቶቹ ፕሮጀክቱ እንዲጓተት፣ በዚህም ምክንያት ተጨማሪ ወጪ ለመጠየቅና ለሙስናና ለብክነት መንገድ የሚከፍቱ ሆነው ቆይተዋል ብለዋል።

ከዚህ በኋላ ፕሮጀክቶቹን የሚቆጣጠረው የፕሮጀክቶቹ ባለቤት መስሪያ ቤቶች ሳይሆኑ የኮንስትራክሽን ቢሮ እንደሚሆንም ጠቁመዋል።

በሶስት ሳምንታት ውስጥ በሚቀርበው ምዘና መሰረትም በሚቀርበው ዝርዝር መረጃ መሰረት በውላቸው  መሰረት ያላጠናቀቁ የሥራ ተቋራጮች ውላቸው እንዲቋረጥና በከተማዋ የፕሮጀክት ስራዎች መሳተፍ ከማይችሉ ኮንትራክተሮች ዝርዝር ውስጥ እንዲካተቱ የሚደረግ መሆኑንም ተናግረዋል።

እስካሁን ባለው ሂደት የከተማ አስተዳደሩ ከሚመድበው አጠቃላይ አመታዊ በጀት ለኮንስትራክሽን ዘርፉ ከ75 እስከ 80 በመቶ ይወስዳል ያሉት ከንቲባው ይህ የህዝብ ገንዘብ እንዲባክን መንገድ መክፈት የለብንም ሲሉም ተናግረዋል።

በአገሪቱ የሚካሄዱ ፕሮጀክቶች በተለያየ ምክንያት እየዘገዩ በመጀመሪያ ከተያዘላቸው የገንዘብ ወጪ በላይ እንደሚያስወጡ ይታወቃል።

በአዲስ አበባም በተመሳሳይ በርካታ የቤቶችና የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች ከዲዛይን፣ ወሰን ማስከበርና ከኮንትራክተሮች የመፈጸም አቅም ጋር በተያያዘ የፕሮጀክቶች መዘግየት ለተጨማሪ ወጪ እየዳረገ ይገኛል።

ዛሬ በምክትል ከንቲባው የተወሰደው ውሳኔ ከኮንትራክተሮች ጋር በተያያዘ የሚያጋጥመውን የፕሮጀክቶች መጓተት ችግር ለመፍታት ትልቅ እገዛ ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል።