በከተሞች አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚታዩ የመልካም አስተዳደር ችግሮች መፍታት እንዲሚገባ ተገለጸ

59

ሀዋሳ ጥር 3/2011 የከተሞችን የአገልግሎት አሰጣጥ  የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመቅረፍ ለህዝቡ ፍትሃዊ አገልግሎት ለመስጠት በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ የደቡብ ክልል ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ አስታወቀ፡፡

ለሁለት ቀናት የሚቆይ ክልል አቀፍ የምክክር ጉባኤ በሀላባ ቁሊቶ እየተካሄደ ነው፡፡

የቢሮው ኃላፊ አቶ ክፍሌ ገብረማርያም እንደገለጹት ህዝቡ የሚያነሳቸውን የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በመፍታት በሀገሪቱ የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ አጠናክሮ ለማስቀጠል ርብርብ ሊደረግ ይገባል፡፡

በማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት አሰጣጥ፣ በመሰረተ ልማት ማስፋፋትና ተደራሽነት፣ በመሬት ልማትና ማኔጅመንት ዘርፍ በከተማ ጽዳትና አረንጓዴ ልማት ንቅናቄ ዙሪያ ችግሮች መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡

የከተማ መሬት አቅርቦትን ግልጽና ፍትሃዊ በማድረግ ለዘላቂ የከተሞች ልማት ስር ነቀል አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ለማድረግም በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡

በክልሉ ከከተሞች መስፋፋትና ከህዝብ ቁጥር መጨመር ጋር ተያይዞ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች እየጨመሩ መምጣታቸውን ገልጸዋል።

ከኢንደስትሪና አገልግሎት ዘርፍ ማደግ ጋር ተያይዞ የሚመነጨው ቆሻሻና በካይ ነገሮች እየጨመሩ መምጣታቸውን የጠቆሙት ኃላፊው የሚመነጨውን ደረቅና ፍሳሽ ቆሻሻ በአግባቡ ማስወገድ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

በመንግስት ተቋማት በተለይም በማዘጋጃ ቤት የሚሰጠው አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ በክልል ደረጃ የማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት አሰጣጥ ደረጃ በማውጣት ልማዳዊ አሰራሩን ወደ ዘመናዊ አሰራር መቀየር መቻሉን አስረድተዋል፡፡

የሀዋሳ ከተማ ማዘጋጃ ቤት ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ፍቅሩ ተስፋዬ ከተማዋ በጽዳትና ውበት  ጥሩ ተሞክሮ ያላት ብትሆንም ከፍሳሽ ማስወገጃ ቦዮች በቆሻሻ መሞላትና ክዳን አለመኖር በተያያዘ ከህዝቡ ቅሬታ እንደሚነሳ  አመልክተዋል፡፡

ከመሬት ጋር በተያያዘ የፍላጎትና አቅርቦት አለመመጣጠን ችግር መኖሩን የገለጹት አቶ ፍቅሩ ያለውን መሬት በፍትሃዊነት ከማቅረብና መዝግቦ ከመያዝ አንጻር ከህዝቡ ጋር በቅርበት የሚሰራበት አሰራር ተዘርግቷል፡፡

የሀላባ ቁሊቶ ከተማ ማዘጋጃ ቤት ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ አብዱልሀዲ ናስር በበኩላቸው ላለፉት ሁለት ዓመታት የማዘጋጃ ቤቱ ቁልፍ ችግሮችን የመለየት ስራ መከናወኑን አስረድተዋል፡፡

በማዘጋጃ ቤት አገልግሎት ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ አገልግሎት አሰጣጡን ቀልጣፋ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ስራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም