በሐረሪ ክልል ባለፉት አምስት ወራት የተሰበሰበው ገቢ የእቅዱ 55 በመቶ ነው

236

ሀረር ጥር 3/2011 በሐረሪ ክልል ባለፉት አምስት ወራት የተሰበሰበው ገቢ የእቅዱን 55 በመቶ ብቻ መሆኑን የሐረሪ ክልል ገቢዎች ባለስልጣን ገለጸ።

ለገቢው መቀነስም በክልሉ በነበረው የፀጥታ ችግርና የህግ የበላይነት አለመከበሩ እንደ ምክንያትነት ተጠቅሷል።

ግብር መክፈል ከምንም ሁኔታ ጋር የማይገናኝና የዜግነትም ግዴታ በመሆኑ ሁሉም የሚጠበቅበትን  መወጣት እንደሚገባው አንድ አንድ ግብር ከፋዮች ገልፀዋል።

የክልሉ ገቢዎች ባለስልጣን የገቢ አሰባሰብና ክትትል ዋና የስራ ሂደት ባለቤት አቶ አብዱላዚዝ ሱፍያን እንደገለጹት ባለስልጣኑ በክልሉ ከሚገኙ ግብር ከፋዮች  በአምስት ወራት ውስጥ 401 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ ነበር።

ሆኖም በአምስት ወራት የተሰበሰበው 222 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር ወይንም 55 በመቶውን ብቻ ነው፡፡

በዚህም ገቢው 45 በመቶ ሊቀንስ መቻሉን ገልፀው ለዚህም  ዋንኛው ምክንያት   “በክልሉ የሚታየው የህግ የበላይነትን ማስከበር አለማስቻልና በአንድ አንድ ግብር ከፋዮች ዘንድ ደግሞ ግብር እንዳይከፈል የሚደረገው ቅሰቀሳ” መሆኑን ተናግረዋል።

ለውጡን ማስቀጠልና መደገፍ የሚቻለው ግብርን በአግባቡ በመክፈል መሆኑን የተናገሩት አቶ አብዱላዚዝ በግብር ከፋዩ ዘንድ ያለውን የግንዛቤ ክፍተትእና በባለስልጣኑ አሰራሮች ላይ መሻሻል የሚገባቸውን ጉዳዮች ለመቅረፍ ባለስልጣኑ የተለያዩ ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡

በዚህም በባለስልጣኑ የ100 ቀን እቅድ ተዘጋጅቶ ወደ ትግበራ እየተገባ መሆኑን ጠቁመው  ባለስልጣኑም ግብርን በአግባቡ ያልከፈሉትን በየወረዳ የመለየት ስራ ማጠናቀቁንና ወደ እርምጃ ለመግባት በዝግጅት ላይ መሆኑን ተናግረዋል።

በአምስት ወራቱ ውስጥ ከግብር ከፋዩ የተሰበሰበው ገቢም ከቀጥታ ታክስ፣ ታክስ ካልሆነ፣ ከማዘጋጃ ቤታዊና ከሌሎች ዘርፎች መሆኑን ጠቁመዋል።

”ግብር ከምንም ሁኔታ ጋር የማይገናኝና የዜግነት ግዴታ በመሆኑ ሁሉም የሚጠበቅበትን ግብር መክፈል ይገባል’ ያሉት ደግሞ ወይዘሮ የምስራች ወንድሙ ‘አሁንም ድረስ የምከፍለው ግብር አቅሜንና ገቢዬን ያገናዘበ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

ግብርን በወቅቱ መክፈል ለአገር ልማት መፋጠን ፋይዳው ከፍተኛ መሆኑን በመገንዘብ ሁሉም የሚጠበቅበትን እንዲወጣ  ጠቁመዋል፡፡

በአነስተኛ የኤሌክትሮኒክስ እቃዎች ስራ ላይ የተሰማሩት አቶ መሀመድ አብዱሌ  በበኩላቸው ቅሬታ እንኳን ሲፈጠር ከባለስልጣኑ ጋር በመነጋገር ችግሮቻቸው እየተፈቱ መሆኑንና የሚጠበቅባቸውን ግብር መክፈላቸውን ገልጸዋል።

ግብር ጠቀሜታው ለአገርና ለራስ ልማት በመሆኑ ሁሉም በጊዜው መክፈል እንደሚገባው መልዕክት አስተላልፈዋል።

በሐረሪ ክልል 13ሺ 161 ግብር ከፋዮች ይገኛሉ።