ፖሊስ "ስለ አባይ እሮጣለሁ" በሚል መሪ ቃል ነገ ለሚካሄደው ሩጫ ሰላማዊነት ዝግጅት ማድረጉን ገለጸ

63
አዲስ አበባ ግንቦት 18/2010 "ስለ አባይ እሮጣለሁ" በሚል መሪ ቃል ነገ በአዲስ አበባ የሚካሄደው ሩጫ በሰላም እንዲጠናቀቅ ዝግጅት ማድረጉን ፖሊስ አስታወቀ። በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት የተዘጋጀውና መነሻና መድረሻውን መስቀል አደባባይ ያደረገው ሩጫ ነገ ይካሄዳል። የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው በርካታ ቁጥር ያለው ነዋሪ የሚሳተፍበት ሩጫ በሰላም እንዲጠናቀቅ ቅድመ ዝግጅት አጠናቆ ወደ ስራ ገብቷል። ከዚህ ቀደም በርካታ ህዝብ በብዛት የተሳተፈባቸው ተመሳሳይ ሩጫዎች በሰላም እንዲጠናቀቁ ነዋሪው፣ የሩጫው ተሳታፊዎችና የፀጥታ አካላት ጉልህ ሚና እንደነበራቸው አስታውሶ «ስለ አባይ እሮጣለሁ» በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀው ሩጫም በሰላም እንዲጠናቀቅ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የፀጥታ አካላት ጋር ተቀናጅቶ እየሰራ መሆኑን አስታውቋል፡፡ ሩጫው በሚካሄድበት ስፍራ ስለታማም ሆነ ማንኛውንም አይነት የጦር መሳሪያ ይዞ መግባት ፍፁም የተከለከለ ነው ያለው ኮሚሽኑ የሩጫው ተሳታፊዎች ፀጥታው የጋራ ጉዳይ መሆኑን ተገንዝበው ወደ መሮጫ ስፍራ ሲገቡ ለፍተሻ እንዲተባበሩ ጥሪውን አስተላልፏል፡፡ ውድድሩ እስኪጠናቅ ከቦሌ ፍላሚንጎ ወደ መስቀል አደባባይ መግቢያ ዋና መንገድ፣ ከባምቢስ ወደ መስቀል አደባባይ መግቢያ ዋና መንገድ፣ ከብሄራዊ ቤተ-መንግስት ወደ እስጢፋኖስ ቤተክርስቲያን፣ ከብሄራዊ ቴአትር በለገሃር መብራት ወደ ስታዲየም፣ በሐራምቤ ሆቴል ጋንዲ ሆስፒታል ወደ መስቀል አደባባይ መግቢያ ዋና መንገድ፣ ከ4ኛ ክፍለ ጦር ወደ መስቀል አደባባይ መግቢያ ዋና መንገድ፣ ከልደታ ቤተክርስቲያን ወደ ሜክሲኮ አደባባይ መግቢያ ዋና መንገድ፣ ከሜክሲኮ ቄራ እንዲሁም ጎተራ ወደ መስቀል አደባባይ የሚወስዱ መንገዶች ለጊዜው ለተሽከርካሪ ዝግ ይሆናሉ። ከቦሌ ወደ አራት ኪሎ መሄድ የሚፈልጉ አሽከርካሪዎች በኡራኤል በካሳንቺስ አራት ኪሎ እንዲሁም ከመገናኛ ወደ ጦር ኃይሎች መሄድ የሚፈልጉ አሽከርካሪዎች በኡራኤል ካሳንቺስ ታላቁ ቤተ-መንግስት እሪ በከንቱ ቴዎድሮስ አደባባይ ኤክስትሪም ሆቴል ተክለኃይማኖት ጦር ኃይሎችን በአማራጭነት እንዲጠቀሙ መክሯል። ከሳሪስ አቅጣጫ ወደ አራት ኪሎ እና ፒያሳ መሄድ የሚፈልጉ አሽከርካሪዎችም ጎተራ ወሎ ሰፈር አትላስ ሆቴል ኡራኤል ካሳንቺስ አራት ኪሎ ያሉ መንገዶችን በአማራጭነት መጠቀም እንደሚችሉ ኮሚሽኑ ገልጿል፡፡ ከዛሬ ማታ ጀምሮ  ውድድሩ እስኪጠናቅ ድረስ በውድድር መስመር ግራና ቀኝ ለረዥምም ሆነ ለአጭር ጊዜ ተሽከርካሪ አቁሞ መሄድ ፍፁም የተከለከለ መሆኑን ኮሚሽኑ አስታውቋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በየአካባቢው የተመደቡ የትራፊክ ፖሊስ እና የፀጥታ አካላት የሚሰጡትን ትዕዛዝ ህብረተሰቡ በማክበር የተለመደ ትብብር እንዲያደርግ ጥሪ አስተላልፏል፡፡ የሩጫው ተሳታፊዎች በሚያልፉት አካባቢ የሚኖሩ ነዋሪዎች እንደ ከዚህ ቀደሙ ከፀጥታ ኃይሉ ጎን በመቆም ትብብራቸውን እንዲያጠናከሩም አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ጥሪውን አቅርቧል፡፡ ህብረተሰቡ ለጸጥታ አጠራጣሪ የሆኑ ነገሮች ሲያጋጥሙት እና የፖሊስ አገልግሎት ማግኘት ሲፈልግ በስልክ ቁጥሮች  011-5-52-63-03፣ 011-5-52-40-77፣ 0115-52-63-02፣ 011-1-11-01-11 ወይም በነፃ የስልክ መስመር 991 እና 987 መጠቀም እንደሚችል ኮሚሽኑ ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም