በቱሪስት ቪዛ ከአገር ወጥተው የሚጠፉ ዜጎች ተበራክተዋል-የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር

389

አዲስ አበባ ጥር 3/2011 በቱሪስት ቪዛ በህጋዊ መንገድ ከአገር ወጥተው የሚጠፉ ዜጎች መበራከታቸው ተገለጸ።

ድርጊቱ የህገ-ወጥ ስደት ሌላ ገጽታ እንደሆነና በዚህም ብዙዎች ለእንግልት እየተዳረጉ መሆኑም ተነግሯል።

የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ እንደገለጹት፤ በቱሪስት ቪዛ በህጋዊ መንገድ ከአገር ወጥተው በዚያው ጠፍተው የሚቀሩ ዜጎች ተበራክተዋል።

ሳውዲ ዓረቢያን በመሳሰሉ አገሮች በህገ ወጥ ደላሎች በመታለል በጎብኚ ቪዛ ከአገር የሚወጡ ዜጎች እንግልት እየደረሰባቸው መሆኑንም ነው የተናገሩት።

ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ከኢሚግሬሽንና ዜግነት ጉዳዮች ዋና መምርያ፣ ከፍትህ አካላት፣ ከፌደራል ፖሊስና ከኢትዮጵያ አየር መንገድ የተውጣጣ የጋራ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ እየተሰራ መሆኑንም አክለዋል።

ስርዓቱ ህጋዊ መስመር እንዲይዝ ሲባል በጎብኚ ቪዛ ከአገር መውጣት እንደማይቻል ሚኒስትሯ አሳስበዋል ።

በሌላ በኩል ባለፈው ሳምንት የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ ከሳዑዲ ዓረብያ አቻቸው ኢንጂነር አህመድ ቢን ሱሌይማን አል ራጂህ ጋር በሁለቱ አገሮች የጋራ ጉዳዮች ላይ በትብብር ለመስራት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መወያየታቸው ይታወሳል።

በዚህም በተለይም በአገሪቷ የሚሰሩ ኢትዮጵያዊያን ሠራተኞች መነሻ የደመወዝ ወለል መጠን 1 ሺህ የሳዑዲ ሪያል እንዲሆንና የሠራተኛውና የአሰሪው መብት በሚጠበቅበት ሁኔታ ላይም መግባባት መድረሳቸውንም እንዲሁ።

በተለይ በሳዑዲ የሚሰሩ ኢትዮጵያዊያን ሠራተኞች መነሻ የደመወዝ ወለል መጠንን በሚመለከትም ከአገሪቷ መንግስት ጋር ስምምነት ላይ ሳይደረስ ለረዥም ጊዜ ቆይቷል።

ለዚህም በውጪ አገራት ስምሪት ላይ የተሰማሩና በሁለቱም አገራት ያሉ ህገ-ወጥ ኤጀንሲዎች ከሳዑዲ ዓረቢያ ጋር በመነጋገር ኢትዮጵያዊያን ሠራተኞች መነሻ የደመወዝ ወለል መጠን 850 ሪያል እንዲሆንና ለኤጀንሲዎቹ 3 ሺ 375 ሪያል ኮሚሽን እንዲከፈል ተፈራርመው ነበር።

ይሁንና የኢትዮጵያ መንግስት ከሳዑዲ መንግስት ጋር በመነጋገር ሁለቱ አገራት ባላቸው ወዳጅነት ምክንያት የዜጎችን መብትና ደህንነት ለመጠበቅ እንዲቻል ስምምነት ላይ በመደረሱ መነሻ የደመወዝ ወለል መጠን 1 ሺህ የሳዑዲ ሪያል እንዲሆን ተደርጓል ብለዋል።

በአገራቱ መካከል የተፈረመውን የሠራተኛ ስምምነት ውል ተግባራዊ ለማድረግም ከሁለቱም አገራት የተውጣጣ የባለሙያዎች ቡድን መቋቋሙንና በየስድስት ወሩ እየተገናኘ አፈጻጸሙን የሚገመግም መሆኑንም ሚኒስትሯ ገልጸዋል።