ኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ በዓለም አቀፍ የዩኒቨርሲቲዎች እግር ኳስ ውድድር ላይ ይሳተፋል

331

አርባምንጭ ጥር 3/2011 ኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ ቻይና በምታዘጋጀው ዓለም አቀፍ የዩኒቨርሲቲዎች እግር ኳስ ዉድድር ላይ የአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎችን በመወከል እንደሚሳተፍ ተገለጸ ፡፡

የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ስፖርት ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ አባይ በላይሁን ለኢዜአ እንደገለጹት በቀጣዩ ዓመት ህዳር ወር ቻይና ለመጀመሪያ ጊዜ ዓለም አቀፍ የዩኒቨርሲቲዎች እግር ኳስ ውድድር ታዘጋጃለች ፡፡

የአፍሪካ ስፖርት ማህበር ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር መቀሌ ላይ ባዘጋጀው 9ኛው የአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች እግር ኳስ ውድድር ላይ 26 የአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ተሳትፊ እንደነበሩ አስታውሰዋል ፡፡

በዚሁ ውድድር ኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ አሸናፊ በመሆኑ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚዘጋጀው መድረክ የአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎችን በመወከል በቀጥታ ይሳተፋል ፡፡

የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ መምህርና የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ስፖርት ማህበር ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ከሳቴ ለገሠ በበኩላቸው ኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ በውድድሩ ውጤታማ ለመሆን በቅርቡ ልምምድ እንደምጀምር ጠቁመዋል ፡፡

ወጪው ሙሉ በሙሉ በአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ስፖርት ማህበር የሚሸፈን ሲሆን ተወዳዳሪዎችም በአካላዊ ብቃት ፣ በቴክኒክና በስነ-ልቦና ብቁ እንዲሆኑ ማህበሩ የቴክኒክ ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡

ቻይና በምታዘጋጀው የዓለም ዩኒቨርሲቲዎች እግር ኳስ ውድድር ዩኒቨርሲቲው መሳተፉ ለአገሪቱ የገጽታ ግንባታ አዎንታዊ ድርሻ እንደሚኖር የጠቆሙት ደግሞ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ስፖርት አካዳሚ ዳይሬክተር ዶክተር ቾንቤ አናጋው ናቸው ፡፡

የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ማህበር በ2011 እቅዱና በቀጣይ አቅጣጫዎቹ ላይ ያተኮረ ውይይት ባለፈው ሳምንት በአርባምንጭ ማድረጉ ይታወሳል፡፡