በመጪው እሁድ በሃዋሳ የአምስት ኪሎ ሜትር የእግር ጉዞ ይካሄል

67

ሀዋሳ ጥር 3/2011 ከተሽከርካሪ ነጻ የሆኑ መንገዶች ቀንን ምክንያት በማድረግ በመጪው እሁድ በሃዋሳ የአምስት ኪሎ ሜትር የእግር ጉዞ ይካሄል፡፡

የክልሉ ጤና ቢሮ ሃላፊ አቶ አቅናው ካውዛ በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት የእግር ጉዞው "ጤናማ የአኗኗር ዘይቤ ለጤናማ ህይወት" የሚል መሪ ቃል አንግቧል፡፡

ስኳር፣ ካንሰር፣ ልብና የመተንፈሻ አካላትን ጨምሮ ሌሎች ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ባለማድረግና ጤናማ ባልሆነ የአመጋገብ ዘዴ የሚመጡ ናቸው፡፡

ከተሸከርካሪ ነጻ መንገዶች ቀንን የእግር ጉዞ በማድረግና ያለተሸከርካሪ በመንቀሳቀስ ችግሩን ለመቅረፍ የተጀመረው የንቅናቄ ስራ ውጤታማ እንዲሆን በትምህርት ቤቶችም እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

ለብስክሌት ምቹ የሆነውን የሃዋሳ ከተማ አቀማመጥ በመጠቀምም ከዚህ ቀደም የነበረውን የብስክሌት አጠቃቀም ለማስጀመር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየሰሩ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ፕሮግራሙን የተሳካ ለማድረግ ቢሮው ከክልሉ ባህል ፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮና ከሃዋሳ ከተማ አስተዳደር ጋር በቅንጅት እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የክልሉ ባህል ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ ሰብለጸጋ አየለ በበኩላቸው የአካል ብቃት እንቅስቃሴው ሰላማዊ ግንኙነትን በመፍጠር ለከተማዋ ገጽታ ግንባታ ከፍተኛ ድርሻ ይኖረዋል፡፡

''ፕሮግራሙን በቀጣይ በትላልቅ የክልሉ ከተሞች በማካሄድ የቱሪዝም እንቅስቃሴውን እንዲያግዝ ይደረጋል'' ብለዋል፡፡

በመጪው እሁድ ጥር 5 በሚካሄደውና 15 ሺ የሚሆኑ የከተማዋ ነዋሪዎች ይሳተፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የገለፁት ደግሞ የክልሉ ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ገልገሎ ገዛኸኝ ናቸው፡፡

ከጠዋቱ 12 ሰዓት ላይ መነሻውን ወልደአማኑኤል አደባባይ የሚያደርገው የአምስት ኪሎ ሜትር የእግር ጉዞ ማጠቃለያው ሲዳማ ባህል አዳራሽ እንደሚሆን ታውቋል፡፡

የደም ግፊት፣ የስኳር መጠን፣ የካንሰር ምርመራ፣ ጤናማ ክብደትና የተለያዩ የምክር አገልግሎት ለመስጠት የጤና ተቋማት ዝግጅት ማድረጋቸውም ታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም