በትግራይ ክልል የማዕድን ክምችትን ጥቅም ላይ ለማዋል የሚደረገው ክትትልና ቁጥጥር አነስተኛ መሆኑን ተገለጸ።

80

መቀሌ ጥር 3/2011 በትግራይ ክልል ያለውን የከርሰ ምድር የማዕድን ክምችት በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲውል ለማድረግ የሚደረገው ክትትልና ቁጥጥር አነስተኛ መሆኑን የትግራይ ክልል ምክር ቤት የኢኮኖሚ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገለጸ።

በችግሩ ምክንያት ባለፉት ስድስት ወራት ከወርቅ ክምችት ብቻ መሰብሰብ ከነበረበት 20 በመቶ ብቻ ተግባራዊ መደረጉ ታውቋል።

የትግራይ ክልል ምክር ቤት የኢኮኖሚ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የክልሉን የማዕድንና ኢነርጂ ኤጀንሲ የስድስት ወራት የስራ እንቅስቃሴ ሪፖርት ላይ ትናንት ውይይት አድርጓል።

በውይይቱ ወቅት የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ዕጻይ እምባዬ እንዳሉት፣ የማእድን ዘርፉ በተቀመጠለት እቅድ እንዳይተገበር የኤጀንሲው የስራ ኃላፊዎች የሚያደርጉት ክትትልና ቁጥጥር አነስተኛ ነው።

ይህም መንግስት ከዘርፉ ማግኘት የሚገባውን ገቢ እንዳያገኝ እንቅፋት መፍጠሩን አመልክተዋል፡፡

ኤጀንሲው በተያዘው የበጀት ዓመት 10 ኩንታል ወርቅ ለመሰብሰብ ማቀዱን የገለጹት ሰብሳቢው በተጠናቀቀው ግማሽ በጀት ዓመት ወደ ብሄራዊ ባንክ ተሰብስቦ ገቢ የተደረገው የወርቅ መጠን ከሁለት ኩንታል ያነሰ ነው፡፡

ይሄም ከተያዘው ዕቅድ ጋር ሲነጻጸር 20 በመቶ ብቻ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

በኤጀንሲው የሚታየው መሰረታዊ ችግር ባለው የሰው ሃይል ወደ ታች ወርዶ ተገቢውን ቁጥጥርና ክትትል አለማድረግ መሆኑን አቶ ዕጻይ ተናግረዋል።

ማዕድን በማምረት የተሰማሩ ግለሰቦችና ባለሃብቶች ከተፈቀደላቸው ቦታ ውጭ መስራት፣ ያመረቱትን የወርቅ መጠን ያለማሳወቅ፣ አምራቾች ወደ ብሔራዊ ባንክ በወቅቱ ማስገባታቸውን ያለመከታተል በኤጀንሲው ከታዩት ችግሮች መካከል ተጠቃሽ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

አምራቾች  የሚያከናውኑዋቸው ተግባራት በአካባቢ ጥበቃ ላይ ተፅእኖ የማያስከትሉ መሆናቸውን ያለመከታተል ሌላው በዘርፉ የሚስተዋል ችግር መሆኑ ተመላክቷል፡፡

በቀጣዮቹ ስድስት ወራት ችግሮችን በመፍታት የተሻለ ገቢ ለማስገባት የኤጀንሲው አመራሮች መንቀሳቀስ እንደሚገባቸው በውይይቱ ላይ ተገልጿል።

የኤጀንሲው ተወካይ አቶ መሓሪ ወልደዮሐንስ በበኩላቸው ኤጀንሲው ባለው የሰው ኃይል እጥረት ምክንያት ወደ ታች ወርዶ ተገቢውን ክትትልና ቁጥጥር ማድረግ እንዳልተቻለ አስታውቀዋል፡፡

በኤጀንሲው የማምረቻ ቦታ ተሰጥቷቸው ወርቅም ሆነ ሌሎች ማዕድናትን በህጋዊ መንገድ የሚያመርቱና የሚሰበስቡትን ህጋዊ ካልሆኑት የመለየት ስራ እየተሰራ መሆኑን  አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም