በተንታ ከተማ በተሽከርካሪ አደጋ የአምስት ሰዎች ሕይወት አለፈ

109

ደሴ ጥር 3/2011 በደቡብ ወሎ ዞን ተንታ ከተማ በደረሰ የተሽከርካሪ አደጋ የአምስት ሰዎች ህይወት ማለፉን ፖሊስ አስታወቀ።

የወረዳው ፖሊስ ጽህፈት ቤት የመንገድ ትራፊክ ደህንነት አስተባባሪ ኢንስፔክተር አንዳርጋቸው ሙሉ ለኢዜአ እንደገለጹት አደጋው የደረሰው ትናንት ከቀኑ 11 ሰዓት አካባቢ ነው።

የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 3 -92998 አማ የሆነ የጭነት ተሽከርካሪ  ከተፈቀደለት ውጭ ሰዎችን ጭኖ ከተንታ ወደ ደሴ በመጓዝ ላይ እንዳለ ከትራፊክ እይታ ለማምለጥ ፍጥነት ጨምሮ ሲጓዝ ነው።

የሟቾች አስክሬን ወደ ቤተሰቦቻቸው መላኩን የተናገሩት ኢንስፔክተር አንዳርጋቸው፣ ከባድ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው 10 ሰዎች በደሴ ሪፈራል ሆስፒታል የሕክምና እርዳታ እየተደረገላቸው መሆኑን አስረድተዋል።

"በአደጋው ህይወታቸው ያለፈና የአካል ጉዳት የደረሰባቸው የደሴ ከተማ ነዋሪዎች በተንታ የሐሙስ ገበያ ውለው በመመለስ ላይ ነበሩ" ብለዋል።

ፖሊስ አደጋውን ያደረሰውን አሽከርካሪ እየፈለገ መሆኑን ገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም