የደገህቡር ከተማ የ24 ስዓት የመብራት አገልግሎት ተጠቃሚ ሆነች

132

ጅግጅጋ ጥር 3/2011በሶማሌ ክልል ደገሃቡር ከተማ የ24 ስዓት የመብራት አገልግሎት ተጠቃሚ መሆኗን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ።

በአገልግሎቱ የሶማሌ ክልል ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ አንተነህ መላኩ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት ከተማዋ የአገልግሎቱ ተጠቃማ የሆነችው ለሦስት ዓመታት የተካሄደው ፕሮጀክት በመጠናቀቁ ነው።

በዚህም ከጅግጅጋ ወደ ከተማ የተከናወነው የመብራት ዝርጋታና የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ግንባታ ፕሮጀክት ለአገልግሎት በቅቷል።

በከተማዋ የተዘረጋው መሥመር 410 የኤሌክትሪክ ኃይል ተሸካሚ ኮንክሪት ምሶሶዎች ተከላ መከናወኑን አስታውቀዋል።

ፕሮጅክቱ ከተማዋን ጨምሮ ከከተማው በ120 ስኩየር ኪሎ ሜትር ርቀት የሚገኙ ጉነገዳ፣ ደገህመዳው፣ ከና አዋሬ የወረዳ ከተሞች እንዲሁም ሁለት ገጠር ቀበሌዎች ተጠቃሚ ይሆኑበታል።

ከጅግጅጋ ወደ ከተማዋ የተዘረጋው ኤሌክትሪክ ኃይል 132 ሺህ ቮልት አቅም እንዳለውም ተናግረዋል፡፡

የደገህቡር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሐሰን መሐመድ የፕሮጀክቱ መጠናቀቅ የነዋሪዎችን የኃይል አቅርቦት ጥያቄ በዘላቂነት እንደሚፈታ አመልክተዋል፡፡

የኃይል አቅርቦቱ በጀረር ዞን ያለውን የእንስሳት ተዋፅኦ ሀብትና የግብርና ምርት ውጤቶችን ለሚጠቀሙ ፋብሪካዎችና ኢንዱስትሪዎች ፋይዳ እንዳለው አስረድተዋል፡፡

የከተማዋ የኤሌክትሪክ ኃይል የደንበኞች አገልግሎት ሥራ አስኪያጅ አቶ አብዮት አበራ በከተማው 1 ሺህ 400 ደንበኞችን መመዝገባቸውን አስታውቀዋል፡፡

ፕሮጀክቱ ለከተማዋ በጄኔሬተር በወር  የሚወጣውን ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ የናፍታ ወጪ እንደሚያስቀርም ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም