ጎንደር ዩኒቨርሲቲ የአገር አቀፍ ጥራት ልዩ ተሸላሚ ሆነ

59

አዲስ አበባ ጥር 3/2011 ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ለሶስተኛ ጊዜ የአገር አቀፍ የጥራት ሽልማት ልዩ ተሸላሚ ሆነ።

የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት ስድስተኛ ዙር የጥራት ሽልማት ትናንት ምሽት በብሔራዊ ቤተ-መንግስት ተካሂዷል።

በሽልማትና ዕውቅና ሥነ-ሥርዓቱ ላይ 40 ድርጅቶችና ተቋማት የምስክር ወረቀትና የዋንጫ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

ጎንደር ዩኒቨርሲቲ፣ ሐረር ቢራ አክሲዮን ማህበር እና አማራ መልሶ ማቋቋምና ልማት ድርጅት የአንደኛ ደረጃ ዋንጫ ተሸላሚ ሲሆኑ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ለተከታታይ ሶስት ዓመታት የጥራት ደረጃውን ጠብቆ አሸናፊ በመሆኑ የልዩ ዋንጫ ተሸላሚ ሆኗል።

በውድድሩ ላይ ከ336 በላይ ድርጅቶች እንዲመዘገቡ ጥሪ የተደረገ ቢሆንም የተመዘገቡት 52 ነበሩ።

ከነዚህ ውስጥ 21 በአምራች፣ አምስት በአገልግሎት፣ አራት በከፍተኛ ትምህርት፣ አምስት በጤና እና አምስት በግንባታ ዘርፍ የተሰማሩ፤ በድምሩ 40 ተቋማት እስከመጨረሻው በውድድሩ የዘለቁ ናቸው።

የሽልማቱ ዋና ዓላማ በኢትዮጵያ አምራቾችና አገልግሎት ሰጪዎች እንዲሁም በግንባታ ዘርፍ የተሰማሩ ድርጅቶች ለጥራት የሚያደርጉትን ስራ ማበረታታት መሆኑ በስነ-ስርዓቱ ወቅት ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት የበላይ ጠባቂ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የጥራት ጉዳይ የሥነ-ልቦናና የፈረጠመ የኢኮኖሚ የበላይነት እንዲሁም የበለፀገ ማህበረሰብ መገለጫዎች ናቸው ብለዋል።

የምርትና አገልግሎት ጥራትን ለማስጠበቅና ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ከደረሱበት የጥራት ደረጃ ለመድረስ ጠንክሮ መስራት እንደሚገባም አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት በ2000 ዓ.ም በዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከልና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ትብብር የተቋቋመ ነው።

እስካሁን 49 ድርጅቶችና ተቋማት የድርጅቱን የልዕቀት ማዕረግ የዋንጫ ሽልማት አግኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም