በግብር አከፋፈል ስርአቱ የሚወጡ ደንብና መመሪያዎች ግንዛቤ ላይ መሰራት አለበት ተባለ

83

አዲስ አበባ ጥር 2/2011በኢትዮጵያ በግብር አሰባሰብ ስርአት የሚወጡ ደንቦችና መመሪያዎች ለግብር ከፋዩ ግልጽ አለመሆን ለገቢ አሰባሰቡ ማነስ ምክንያት ሆኗል  ተባለ።

የኢትዮጵያ ብሮድካስት ኮርፖሬሽን ከገቢዎች ሚኒስቴት ጋር በመተባበር ያዘጋጀውና በግብር አከፋፈል ዙሪያ ያሉ ችግሮችና መፍትሔዎቻቸው ላይ ያተኮረ  የፓናል ውይይት ዛሬ ተካሂዳል።

በፓናል ውይይቱ የንግዱ ማህበረሰብ ተወካዮች፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ ምህራን፣ የመንግስት ኃላፊዎችና ሌሎች ግለሰቦች ተገኝተዋል።

በገቢዎች ሚኒስቴር የታክስ ትራንስፎርሜሽን ጽህፈት ቤት ሃላፊ  ዶክተር አዲሱ ታምሬ "ግብር የማን ጉዳይ ነው" በሚል ለውይይቱ መነሻ የሚሆን ጹህፍ አቅርበዋል።

በዚሁ ፅሁፋቸው እንዳመለከቱትም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የታክስ ገቢ ከአገራዊ ምርት ያለው ድርሻ እየቀነሰ መምጣቱን ገልፀዋል።

አሁን ያለው የ11 በመቶ የታክስ ገቢ ከአመታዊ አጠቃላይ ምርት ጥምርታ ከአፍሪካ አገራት ጋር ሲነጻጸር ዝቅተኛ መሆኑንም ጠቅሰዋለ።

በዶክተር አዲሱ ታምሬ ገለፃ መሰረት ባለፉት ሶስት አመታት ብቻ 82 ቢሊዮን ብር ገቢ ሳይሰበሰብ ቀርቷል።

አገራዊ አለመረጋጋት፣ ህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር፣ ደረሰኝ የመቀበል ልማድ አለማደግ፣ የሽያጭ ማሳነስ፣ የተጭበረበረ ደረሰኝና ሌሎች ህገ ወጥ አሰራሮች የገቢ አፈጻጸሙ እንዲቀንስ ያደረጉ ምክንያቶች ተብለው በጹህፉ ተዘርዝረዋል።

የፓናል ውይይቱ ተሳታፊዎች በግብር አከፋፈል ስርአቱ ያሉ ውስብስብ አሰራሮችን ማዘመንና መፈተሽ እንደሚገባ ነው ያሳሰቡት። 

በተጨማሪም የግብር አሰባሰብ ስርአቱ ወጥ አሰራት የተዘረጋለትና እንደየንግድ አይነቱ ግብር መወሰን እንዳለበትም ተሳታፊዎች አንስተዋል።

ጠንካራ አገር ለመገንባትና ለከፈለው ግብር መብቱን የሚጠይቅ ትውልድ ለመፍጠር በትምህርት ቤት ደረጃ መሰራት እንዳለበትም ሃሳብ ተነስቷል።

የገቢዎች ሚኒስትር ዴኤታ አቶ መሃመድ አብዱ "በመስሪያ ቤቱ ከአሰራር ጋር በተገናኛ መሻሻል አለባቸው ተብለው የተነሱ ጉዳዮችን እንደ ግብአት ወስደን እናስተካክላለን" ብለዋል።

በፓናል ውይይቱ የገቢ ግብር አሰባሰቡን ስርአት ማዘመን የተመለከቱና ግንዛቤ ማስፋት ላይ ሰፊ ሃሳቢች ተነስተዋል።

"ግዴታዬን እወጣለው፣ መብቴን እጠይቃለው" በሚል መሪ ቃል የተቀረፀው አገር አቀፍ የማህበሰረብ የታክስ ንቅናቄ ባለፈ ታህሳስ 12 ቀን 2011 ዓም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድ በተገኙበት በይፋ ተጀምሯል።  

የንቅናቄው ዓላማ አገሩንና ህዝቡን አክብሮ በንፁህ ልቦናና በፍፁም ታማኝነት ግብሩን በወቅቱና በእውነተኝነት የሚከፍል ማህበረሰብ መፍጠር ሲሆን ለመጪው አንድ ዓመት የሚዘልቀ ነው።

በንቅናቄው የሙዚቃ ኮንሰርቶችን፣ ስፖርታዊ ክዋኔዎችን፣ አገር አቀፍ ጉባኤዎችን ጨምሮ በርካታ መርሃ ግብሮች ተግባራዊ ይደረጋሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም