የሰመራ ዩኒቨርሲቲ የሰላም አምባሳደርነቱን ለማረጋገጥ እየሰራ መሆኑን አስታወቀ

78

ሰመራ  ጥር 2/2011 የሰመራ ዩኒቨርሲቲ የመማር ማስተማር ሂደቱን ሰላማዊ ለማድረግ የተቀናጀ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን ፕሬዚዳንቱና በጉዳዩ ላይ የሚሰሩ አካላት ገለጹ።

ዩኒቨርሲቲው ከአገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች መካከል ''የሰላም አምባሳደርነት''ን ማዕረግ ለማግኘት እንደሚሰራም አመልክቷል።

ፕሬዚዳንቱ ዶክተር አደም ቦሪና የዩኒቨርሲቲው የሰላም ኮሚቴና የሰላም አማካሪ ምክር ቤት አባላት ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንዳመለከቱት በዩኒቨርሲቲው የሚካሄደው የመማር ማስተማር ሰላማዊነቱን ጠብቆ እንዲቀጥል እየተደረገ ነው።

የዩኒቨርሲቲውን ሰላም የሚያውኩ ችግሮችን ከምንጫቸው ለማድረቅ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራና ለዚህም አደረጃጀቶች መፈጠራቸውን ፕሬዚዳንቱ አስረድተዋል።

አደረጃጀቶቹ ተማሪዎቹ አገራዊ ለውጡን ለማደናቀፍና የሐሰት መረጃዎች በመልቀቅ ከትምህርታቸው ሊያስተጓጎሏቸው የሚሞክሩ የውጭ ኃይሎችን ግፊት ለመቋቋም እንደሚሰሩም አስረድተዋል።

ተማሪዎቹ ወደ ዩኒቨርሲቲው የመጡበትን ዓላማ ለማሳካት ሰላሙ የተጠበቀ አካባቢ አንደሚያስፈልጋቸው የሚናገሩት ዶክተር አደም፤ በዩኒቨርሲቲው የተመሰረቱት አደረጃጀቶች ለሰላም ዘብ በመቆም ዓላማቸውን እንደሚያስፈጽሙም አመልክተዋል።

የዩኒቨርሲቲው የለውጥና መልካም አስተዳደር ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ እንድሪስ ሰይድ ተማሪዎች ከትምህርታቸው የሚያዘናጉና ወዳልተፈለጉ ሁኔታዎች እንዲገቡ የሚያደርጉ ሁኔታዎች እንደሚያጋጥሟቸው ያወሳሉ።

ከችግሮቹ መካከል ውስጣዊ ለሆኑት በተማሪዎች ኅብረት አማካይነት በማህበራዊ ድረ-ገጾች ተደራጅተው ፈጥነው መረጃ የሚያገኙበት ሥርዓት መደራጀቱን ገልጸዋል።

አሎ አብዱ የዩኒቨርሲቲው የአምስተኛ ዓመት የኬሚካል ምህንድስና ተማሪና የተማሪዎች ኅብረት ምክትል ፕሬዚዳንት ነው።ኅብረቱ የመማር ማስተማር ሂደቱ ሰላማዊነቱን የጠበቀ እንዲሆን ከማኔጅመንቱ ጋር ተባበሮ እንደሚሰራ ይናገራል።

ተማሪዎች በሀገሪቱ ነባራዊ ሁኔታዎች ላይ መረጃ እንዲኖራቸው ግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን እንደሚያከናውንም አመልክቷል።

በዚህም ከብሄርና ከሃይማኖት ጋር ተያይዘው የሚከሰቱ ግጭቶችን የሚያስትሉትን አደጋ እንዲገነዘቡት ይደረጋል ብሏል።

የኤሌክትሪካል ምህንድስና የአራተኛ ዓመት ተማሪና በዩኒቨርሲቲው የሰላም ፎረም የሰላም እሴት አስተምህሮ ዘርፍ ኃላፊ ጌታነው ተስፋው “ትምህርቱ በአክቲቪስቶችና ፖለቲከኞች ጣልቃ ገብነት እንዳይበላሽ እያደረግን ነው” ይላል።

ተማሪ ናሲ ጌታቸው ደግሞ የኅብረቱ የሴቶች ዘርፍ ኃላፊ ሆና ትሰራለች።በትምህርቷም በሥነ ሕይወት ሦስተኛ ዓመት ደርሳለች።ወደ ዩኒቨርሲቲው የመጡበትን ዓላማ መዘንጋት በተለይ በሴት ተማሪዎች ዘንድ እንደማይታይ ትገልጻለች።

ዩኒቨርሲቲው ለሰላም ጉዳይ ባዘጋጀው ኮሚቴ ውስጥ የአገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች ያሉበት አማካሪ ኮሚቴ ተዋቅሯል

የአፋር ክልል ሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ሰብሳቢ ሼክ መሐመድ ደረሳ ተማሪዎቹ ወደ ሰመራ የመጡበትን ዓላማ ትተው ለግጭት የሚዳርጓቸው ችግሮች እንዳይከሰቱ ለሰላም መስፈን የእምነት ተቋማት ትኩረት ሰጥተው እየሰሩ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የአፋር አገረ ስብከት የሰበካ ማደራጃ መምሪያ ኃላፊ ርዕሰ ደብር ሰለሞን ኃይሌ የኮሚቴው አባል በመሆን አገልግሎት እየሰጡ ነው።

ኮሚቴው  አግባብ ካላቸው አካላት ጋር በመቀናጀት በዩኒቨርሲቲው ሰላማዊ የትምህርት ሂደት እንዲቀጥል ጥረት እያደረገ መሆኑን ይናገራሉ።

የሰመራ ዩኒቨርሲቲ ከተመሰረተ 10 ዓመታት አስቆጥሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም