የአማራ ክልል የ2011 የበጋ ወቅት የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ሥራ ተጀመረ

939

ሰቆጣ  ጥር 2/2011 የክልሉ የ2011 የበጋ ወቅት የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ሥራ መጀመሩን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አስታወቀ፡፡

ሥራው በዋህግህምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ጋዚግባ ወረዳ በደብረ ወይላ ቀበሌ ዛሬ ጀምሯል፡፡

በመርሐ ግብሩ ከጥር 4 ነጥብ 6 ሚሊዮን ህዝብ ይሳተፋል፡፡

የቢሮው ምክትልኃላፊ አቶ ማርቆስ ወንዴ ሥራው በይፋ ሲጀመር እንደተናገሩት በዘንድሮው የተቀናጀ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ሥራ ከ6 ሺህ በላይ ተፋሰሶች ይለማሉ።

በመርሐ ግብሩ ከሚለሙ ተፋሰሶች 380 የሚሆኑት ከዚህ በፊት የልማት ሥራ ያልተከናወነባቸው አዳዲስ ተፋሰሶች መሆናቸውን አመልክተዋል።

ሥራው የክልሉ በህይወት የመኖር የህልውና ዋስትና ተደርጎ በተቀናጀ አግባብ እንዲተገበርም ይደረጋል ብለዋል።

በመልማት ላይ ያሉትን ተፋሰሶችን ውጤታማ ለማድረግ ኅብረተሰቡ እንክብካቤና ጥበቃውን እንዲያከናውን አሳስበዋል፡፡

መርሐ ግብሩ ከጥር 2/2011 ጀምሮ ለ25 ተከታታይ ቀናት የሚከናወን ሲሆን፣ በሥራውም 4 ነጥብ 6 ሚሊዮን ህዝብ  ይሳተፋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ካባ ዑርጌሳ  የተፈጥሮ ሃብትን በአግባቡ ያለመጠቀም ለደን መመናመና በረሃማነት መስፋፋት ምክንያት መሆኑን ገልጸዋል።

የግብርና ምርትና ምርታማነት በመቀነሱ ኅብረተሰቡ በተረጋጋ መንገድ ህይወቱን እንዳይመራ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡

በሥራው የኅብረተሰቡን ተሳትፎ በማሳደግ የዜጎችን ተጠቃሚነት ማሳደግ እንደሚገባ የተናገሩት ሚኒስትር ዴኤታው፣ አርሶ አደሩ የባለሙያዎችን ምክረ ሃሳብ እንዲተገብር አስገንዝበዋል።

የዋግህምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ በሪሁን ኪዳነማርያም በበኩላቸው ለሥራው ውጤታማነት ኅብረተሰቡ በትጋት እንዲሰራ ጠይቀዋል።

በዞኑ የደን መመናመንና የድርቅ ተጋላጭነት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ችግር መፍጠሩን ተናግረዋል።

ሥራው ምርታማነትን በሚያሳድግና የምግብ ዋስትና ችግርን በሚፈታ መንገድ እንደሚተገበር አመልክተዋል፡፡

የደብረ ወይላ ቀበሌ ነዋሪው ወጣት ቢረስ ደምሴ ከሁለት ዓመታት በፊት በ13 ወጣቶች የተጀመረው የተፋሰስ መስኖ ልማት በሚያስገኝላቸው ገቢ ራሳቸውን እያስተዳደሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የዚሁ ቀበሌ ነዋሪ አረጋሽ ወዳጆ በበኩላቸው ካለፉት አምስት ዓመታት ጀምሮ በመርሐ ግብሩ ተሳታፊ መሆናቸውን ገልጸው በተከናወነው ሥራ ተጨባጭ ውጤት መገኘቱን ተናግረዋል፡፡

በመርሐ ግብሩ ላይ የፌደራል፣ የክልል፣ የዞንና ወረዳ አመራሮች፣ ባለሙያዎች እንዲሁም የቀበሌው ነዋሪዎች ተገኝተዋል።