አየርላንድ በኢትዮጵያ ባህላዊና ታሪካዊ ቅርሶች ጥበቃ ላይ በትብብር እንደምትሰራ ገለፀች

77

ላሊበላ ጥር 2/2011 አየርላንድ በኢትዮጵያ ባህላዊና ታሪካዊ ቅርሶች ጥበቃና እንክብካቤ ላይ በትብብር እንደምትሰራ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚንስትር ሊኦ ቫራድካር አረጋገጡ።

በኢትዮጵያ የሚገኙት ጠቅላይ ሚንስትሩ ዛሬ የደብረ ሮሃ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስትያናትን ጎብኝተዋል።

በጉብኝቱ ላይ የባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ሚንስትሯ ዶክተር ሂሩት ካሳውና የቤተ ክህነት ኃላፊዎች ተገኝተዋል። 

ጠቅላይ ሚኒስትር ሊኦ ቫራድካር በጉብኝቱ ወቅት እንዳሉት ከወጣትነት ዘመናቸው ጀምሮ የኢትዮጵያን ባህል፣ ወግና ታሪካዊ ቅርሶች ለማየት የነበራቸው የቆየ ጉጉት በመሳካቱ መደሰታቸውን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ በዓለም ቅርስነት የተመዘገቡ ታሪካዊና ባህላዊ ቅርሶችን ጥበቃና እንክብካቤን ለማጠናከር አገራቸው ያላትን ልምድና ዕውቀት ለማካፈል በትብብር ትሰራለች ብለዋል።

በተለይም እንደ ላሊበላ ዓይነት ዓለም አቀፍ ጎብኚዎች መዳረሻ የሆኑ ቅርሶችን ለምጣኔ ኃብታዊ ዕድገት፣ ለገጠር ቱሪዝምና የስራ እድል ፈጠራ ማዋል እንዲቻል የአየርላንድ መንግስት በትብብር እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

"ዘላቂነት ያለው የቅርሶች እንክብካቤ በማድረግ ረገድም ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በጋራ ስምምነት በማድረግና ፕሮጀክቶችን በመቅረጽ እንሰራለን" ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

ይህም የሁለቱን አገራት ግንኙነት በይበልጥ ለማጠናከር እንደሚረዳ አክለዋል። 

የባህል፣ቱሪዝምና ስፖርት ሚንስትሯ ዶክተር ሂሩት ካሳው በበኩላቸው የጠቅላይ ሚንስትሩ ጉብኝት ኢትዮጵያ በታሪክ፣ በባህልና በተፈጥሮ ኃብቶች ላላት ቀዳሚ ደረጃ ዕውቅና የሚሰጥ በመሆኑ ምስጋናቸውን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ከአንድ ቋጥኝ የተፈለፈሉ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስትያናትን ጨምሮ ጥንታዊ የስልጣኔ መገኛ አገር ናት ሲሉም አውስተዋል።

ሚንስትሯ እንደገለጹት አየርላንድ በዩኒስኮ የተመዘገቡ ብርቅ ቅርሶች ባለቤት ብቻ ሳትሆን ቅርሶችን በመጠበቅና ለጎብኚዎች ተደራሽ በማድረግ የተካነች አገር እንደሆነችም በጉብኝቱ ላይ ገልፀዋል። 

ኢትዮጵያም ይህንን ተሞክሮና ልምድ ለመጠቀም  ከአየርላንድ ጋር በባህል፣ ቱሪዝም፣ በገጠር ስራ እድል ፈጠራና በቅርሶች አረንጓዴ ቴክኖሎጂ (Green heritage technology) ዘርፍ የልማት መስኮች በጋራ ለመስራት የጋራ ስምምነት እንደምትፈራረም ተናግረዋል።

በዚህም በቅርቡ የአየር ላንድ ተሞክሮዎችን ለማየትና የትብብር ስራዎችን ለማጠናከር የሚንስትር መስሪያ ቤቱ ልዑካን ወደአየርላንድ እንደሚያቀና ገልጸዋል።

አየርላንድም የቴክኒክና የፋይናንስ ድጋፍ በተለይም ችግር በገጠማቸው የላሊበላ ቅርሶች ጥበቃ ላይ ድጋፍ እንደምታደርግ እምነታቸውን ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ቫራድካር በዛሬው እለት በትግራይ ክልልም ጉብኝት አድርገዋል።

በዚህም በትግራይ ማእከላዊ ዞን ታህታይ ማይጨው ወረዳ በአይሪሽ ድጋፍ የተገነቡ የማህበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማትን ጎብኝተዋል።

የአየርላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ሊኦ ቫራድካር በኢትዮጵያ የሶስት ቀናት የሥራ ጉብኝት ለማድረግ ባለፈው ማክሰኞ ነው አዲስ አበባ የገቡት።

በትናንትናው እለት ከፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴና ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጋር በሁለቱ አገራት የጋራ ጉዳዮች ላይ መክረዋል።

ኢትዮጵያ እና አየርላንድ ረዥም ዘመን ያስቆጠረ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ያላቸው ሲሆን፤ እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር በ2014 የአየርላንድ ፕሬዝዳንት ሚካኤል ሄገንስ ኢትዮጵያን ጎበኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም