ትራንስፎርመር ለማግኘት ክፍያ ብንፈጽምም ማግኘት አልቻልንም….ባለሀብቶችና ወልድያ ዩኒቨርሲቲ

3721

ወልዲያ ግንቦት 18/2010 በወልድያ ከተማ በኢንዱስትሪ መንደር ፋብሪካ የገነቡ ባለሃብቶችና የወልድያ ዩኒቨርሲቲ ትራንስፎርመር ለማግኘት ከሁለት ዓመት በፊት ክፍያ ፈጽመው ቢጠብቁም ማግኘት ባለመቻላቸው መቸገራቸውን ገለፁ።

በኢንዱስትሪ መንደሩ የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ሥራ አስኪያጅ አቶ ደስታው ካሳው ለኢዜአ እንደገለፁት የፋብሪካውን ግንባታ አጠናቀው ከውጭ ያስገቧቸውን ማሽኖች ለመትከል ቢዘጋጁም በትራንስፎርመር ምክንያት እስካሁን ሥራ አለመጀመራቸውን ተናግረዋል።

ትራንስፎርመር እንዲገባላቸው ክፍያ ከፈፀሙ ሁለት ዓመት እንደሞላቸው ገልጸው፣ ማሽኖቹ ለረጅም ጊዜ ያለስራ በመቀመጣቸው ለብልሽት እየተዳረጉባቸው መሆኑን ተናግረዋል።

የፋብሪካው ባለቤት ለግንባታና ለማሽን ግዥ ከ2 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር በላይ ማውጣታቸውን አመልክተው፣ ማሽኖቹ ለባሰ ብልሽት እንዳይጋለጡ ከመስጋትና በስራው ተስፋ በመቁረጣቸው ማሽኖቹን መልሰው ለመሸጥ በሂደት ላይ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡

በወልድያ ዩኒቨርሲቲ የተቋማዊ ልማት ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ይኸነው በላይ በበኩላቸው ተቋሙ አዲስ በመሆኑ ሕንጻዎችን አገልግሎት ላይ ለማዋል ከሦስት ዓመት በፊት ስድስት ትላልቅ ትራንስፎርመሮች እንዲገቡለት ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ቢከፍልም እስካሁን ያገኙት ሦስት ትራንስፈርመር ብቻ መሆኑን ተናግረዋል።

የቀሪዎቹ ትራንስፎርመር መዘግየት ከ15 በላይ ሕንጻዎች የታለመላቸውን አገልግሎት መስጠት እንዳይጀምሩ ምክንያት መሆኑንም ገልፀዋል።

እንደምክትል ፕሬዚዳንቱ ገለጻ፣ ትራንስፎርመሩ እንዲቀርብላቸው ለሚመለከተው የመንግስት አካል ተደጋጋሚ ጥያቄ ቢያቀርቡም መፍትሄ ማግኘት ባለመቻላቸው በመማር ማስተማሩ ላይ ችግር እየተፈጠረ ነው።

በወልድያ ከተማ ንግድ፣ ኢንዱስትሪና ገበያ ልማት ጽህፈት ቤት ሲቪል መሀንዲስ አቶ ንጉስ አያሌው በአንፃሩ የትራንስፎርመር አቅርቦት እጥረት በኢንዱስትሪ መንደሩ በገቡ ባለሀብቶች ላይ ተፅኖ እየፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል።

በወልዲያ ኢንዱስትሪ መንደር 24 ባለሀብቶች የገቡ ሲሆን ከእነዚሁ ውስጥ የግንባታ ሥራቸውን ያጠናቀቁ ሦስት ኢንዱስትሪዎች የኃይል አቅርቦት በማግኘታቸው የማምረት ሥራ መጀመራቸውን አስረድተዋል።

ይሁንና በኢንዱስትሪው የቶርኖ ቤትና የጨርቃጨርቅ ፋብሪካዎች ግንባታ ቢያጠናቅቁም በትራንስፎርመር መዘግየት ምክንያት ሥራ መጀመር አለመቻላቸውን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት የወልድያ ዲስትሪክት ሥራ አስኪያጅ አቶ ዮናስ ጌታቸው በበኩላቸው በእነሱ በኩል የትራንስፎርመር ጠያቂዎችን ማመልከቻ ተቀብለው ለሰሜን ምስራቅ ሪጂን ማሳወቅና እቃው ሲቀርብላቸው ብቻ እንደሚያሰራጩ ተናግረዋል፡፡

ባለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት ለምን እንደዘገየ ባያውቁም የተጠየቁት ስምንት ትራንስፎርመሮች ሰሞኑን ወደዲስትሪከቱ መድረሳቸውን አረጋግጠዋል፡፡

አሁንም ቢሆን ከትራንስፎርመሮቹ ጋር አስፈላጊ ፊውዞችና የመብረቅ መከላከያዎች አብረው መምጣት ባለመቻላቸው ትራንስፈርመሮቹ አገልግሎት እንደማይጀምሩ አብራርተዋል።

ተጨማሪ እቃዎቹ ሲመጡም በመግጠም ስራ እንዲጀምሩ የሚደረግ መሆኑንም አመልክተዋል።

በወልድያ ከተማ ለብዙ ዓመታት ከፍተኛ የኃይል እጥረት የነበረ ቢሆንም ከመጋቢት 2010 ጀምሮ እጥረቱ በአባዛኛው መቃለሉ ይታወቃል ፡፡