በነጎሃ አጽብሃ የምርመራ መዝገብ ተጠርጥረው የተያዙት 33 ተጠርጣሪዎች ዛሬ ፍርድ ቤት ቀርበዋል

54

አዲስ አባባ ጥር 1/2011 በነጎሃ አጽብሃ የምርመራ መዝገብ ላይ የተካተቱና በሰብዓዊ መብት ተጠርጥረው የተያዙት 33 ተጠርጣሪዎች የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 10ኛ የወንጀል ችሎት ዛሬ ቀርበዋል።

በዛሬው የችሎት ውሎ ፖሊስ ''በተጠረጠሩበት የሠብአዊ መብት ጥሰት ላይ የማጣራቸዉ ስራዎች ስላሉኝ ተጨማሪ ጊዜ ይሠጠኝ'' ብሎ ጠይቋል።

የተጠርጣሪ ተከላካይ ጠበቆች በበኩላቸው ''ፖሊስ በየጊዜዉ የሚጠይቀው የምርመራ ጊዜ አግባብነት የለዉም ሊፈቀድለት አይገባም'' ብለዋል።

እስካሁን ፖሊስ በተደጋጋሚም በሚጠይቀው የጊዜ ቀጠሮ ውስጥ ሠራሁ ብሎ የሚያቀርባቸው ምርመራዎች ተመሳሳይ በመሆናቸው የጊዜ ቀጠሮው ሊፈቀድለት አይገባም ሲሉ መከራከሪያ አቅርበዋል።

በችሎቱ ውሎ የተከላከይ ጠበቆች በ30 ተጠርጣሪዎች ፖሊስ የጠየቀውን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ አስመልክቶ የመከራከሪያ ሀሳብ ያቀረቡ ሲሆን ቀሪ የሶስት ተጠርጣሪዎች ክርክር ሳይካሄድ የፍርድ ቤቱ መደበኛ የስራ ሰዓት በመጠናቀቁ ምክንያት ፍርድ ቤቱ የቀሪ ሶስት ተጠርጣሪዎች ክርክር እንዲጠናቀቅ ለነገ ጠዋት 3 ሰአት ከ30 ደቂቃ በይደር ቀጥሯል።

33ቱ ተጠርጣሪዎች በፖሊስ የተያዙት በተለያዩ ግለሰቦች ላይ የሠብዓዊ መብት ጥሠት በማድረስ ፣ በማሠር ፣ በማሠቃየት፣ በመደብደብና ወንዶችን በማኮላሸት ወንጀል ተጠርጥረው ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም