ሰፋፊ የእርሻ ኢንቨስትመንትን የሚያነቃቃ አገር አቀፍ የድጋፍ ማዕቀፍ ተዘጋጀ

3876

አዳማ  ግንቦት 18/2010 በተለያዩ ችግሮች ምክንያት በሚፈለገው መልኩ ውጤት ሳይመዘገብበት የቆየውን የሰፋፊ እርሻ ኢንቨስትመንት በማነቃቃት ወደ ምርታማነት ለማሸጋገር የሚያስችል አገር አቀፍ የድጋፍ ማዕቀፍ ተዘጋጀ።

በሚኒስቴር መዕርግ የኢትዮጵያ ሆርቲካልቸርና ግብርና ኢንቨስትመንት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ያዕቆብ ያላ እንደገለጹት በተለያዩ ክልሎች ለሰፋፊ የእርሻ ኢንቨስትመንት 3 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ተለይቶ 2 ሚሊዮን ሄክታሩ ለባለሃብቶች ተላልፏል ።

“ዘርፉ ካሉበት በርካታ ችግሮች ምክንያት በተጨባጭ የለማው 800 ሺህ ሄክታር መሬት ብቻ መሆኑን ገልጸው ከእዚህም በዓመት የሚገኘው ምርት በአማካይ ከ10 ሚሊዮን ኩንታል የሚበልጥ አይደለም” ብለዋል ።

በዘርፉ የሚታዩትን ችግሮች መፍታት ከተቻለ በመቶ ሚሊዮኖች ኩንታል የሚቆጠር ምርት ከሰፋፊ እርሻዎች ማግኘት እንደሚቻል የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ባለስልጣኑ ላለፈው አንድ ዓመት ዝርዝር የዳሰሳ ጥናት ሲያካሂድ መቆየቱን ተናግረዋል።

የችግሩ ምንጮች በአግባቡ በመለየታቸው በየደረጃው ችግሮቹን በመፍታት ተገቢ ድጋፍ ለማድረግ የሚያስችል ማዕቀፍ ተዘጋጅቶ ጉዳዩ በሚመለከታቸው አካላት እየተመከረበት መሆኑን አስረድተዋል ።

የዳሰሳ ጥናቱን ግኝት ትናንት በአዳማ ከተማ በተዘጋጀው የምክክር መድረክ ላይ ያቀረቡት የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አበራ ሙላት ናቸው።

ምክትል ዳይሬክተሩ እንደገለጹት አዳዲስ ወደ ዘርፉ ለሚገቡ አልሚዎች የተሳለጠ የመሬት አቅርቦት ያለማመቻቸት፣ ለኢንቨስትመንት የተላለፉ መሬቶች በተሟላ ሁኔታ ወደ ልማት ማስገባት አለመቻል፣ የእርሻ ኢንቨስትመንት በሚካሄድባቸው አካባቢዎች ለልማት ምቹ ሁኔታ አለመፍጠር የተስተዋሉ ችግሮች ናቸው።

ከእዚህ በተጨማሪ የአልሚዎቹ ምርትና ምርታማነት ዝቅተኛ መሆን፣ የአካባቢና ማህበራዊ ደህንነትን ማዕከል ያደረገ ዘላቂ ልማት አለማካሄድ ከችግሮቹ መካከል ይጠቀሳሉ።

“አስፈላጊው የገበያ ትስስር በመፍጠር የሎጅስቲክ አገልግሎት እንዲሟላ አለማድረግና ጠንካራ የክትትልና ድጋፍ ስርዓት አለመዘርጋትም የዘርፉ ተግዳሮቶች ናቸው” ብለዋል ።

እንደ አቶ አበራ ገለጻ፣ እያንዳንዱን ችግር ለመፍታት የሚያስችሉ ዝርዝር የመፍትሄ አቅጣጫዎችም በዳሰሳ ጥናቱ የተለዩ ሲሆን ከባለሀብቱ ጋርም ተቀራርቦ ለመስራት ጥረት ይደረጋል።

በዳሰሳ ጥናቱ ላይ ለመምከር በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ባለው የሁለት ቀናት መድረክ ላይ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ ከባለድርሻ አካላት፣ ከባለሃብቶችና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የክልልና የፌዴራል ተቋማት የተወጣጡ የሥራ ኃላፊዎችም ተገኝተዋል።

ባለሃብቶቹ በሰጡት አስተያየት ቸግሮች ባሉበት ሁኔታ ሲሰሩ መቆየታቸውን ገለፀው በአሁኑ ወቅት መንግስት ችግሮቹን ለመፍታት የተጀመረው እንቅስቃሴ ዘርፉን ወደ ተሻለ ምዕራፍ ያሸጋግረዋል የሚል ተስፋ እንዳሳደረባቸው ተናግረዋል ።

በጋምቤላ ክልል 500 ሄክታር መሬት በማልማት ተግባር ላይ የተሰማሩት አቶ እኩች ኡጉል ኡኬሎ በሰጡት አስተያየት “አገር ሰትወረር ጠብመንጃ አንስተን በአንድነት እንደምንዋጋ ሁሉ በፀረ ድህነት ትግሉም እጅ ለእጅ ተያይዘን ከተረባረብን ውጤታማ እንሆናለን” ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት ባለሀብቱ በፈለገው የኢንቨስትመንት አማራጮች እንዲሰማራና ውጤታማ እንዲሆን ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ አድናቆታቸውነ ገልጸዋል።

በውይይት መድረኩ ላይ በእርሻ ኢንቨስትመንት የተሳተፉት ባለሃብቶች በአገር አቀፍ ደረጃ ማህበር አቋቁመው ችግራቸውን ለመፍታትና ምርትና ምርታማነታቸውን ለማሳደግ የሚያስችል አቅም ለመገንባት መግባባት ላይ ይደርሳሉ ተብሎ ይጠበቃል ።

የሰፋፊ እርሻ ኢንቨስትመንት መስፋፋት አገራዊ የኢንዱስትሪ የግብአት ፍላጎት ለማሟላት፣ የአገሪቱን የውጭ ምንዛሬ አቅም ለማሳደግና ለዜጎች ሰፊ የሥራ ዕድል ለመፍጠር ወሳኝ ሚና የሚጫወት መሆኑን በመድረኩ ተመልክቷል።