ኢትዮጵያና ኤርትራን የሚያገናኘው መንገድ ህጋዊ ስርዓት መያዙ ግንኙነታቸውን ያጠናክራል--ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል

79

መቀሌ ጥር 1/2011 በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል የተከፈተው መንገድ  ህጋዊ ስርዓት መያዙ  የሁለቱን ሀገራት ህዝቦች ግንኙነት እንደሚያጠናክረው የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ገለጹ፡፡

ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ የሁመር-ኦምሐጀር መንገድ መከፈትን  ምክንያት በማድረግ   ትላንት ማምሻውን ለጋዜጠኞች  እንደገለጹት የኦምሐጀር መንገድ የተከፈተው ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ቀደም ብለው በደረሱት ስምምነት መሰረት ነው፡፡

የሁለቱም ሃገራት አገናኝ መንገዶች ህጋዊ ስርዓት እንዲይዙ  ማድረጉ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።

"የዛላምበሳ መንገድ መዘጋት ከኦምሐጀር መንገድ መከፈት ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም" ያሉት ዶክተር ደብረፅዮን  ፣ የዛላምበሳ መንገድ የተዘጋው የሁለቱ ሀገራት የመንገድ ግንኙነት ህጋዊ ስርዓት ለማስያዝ  መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የዛላምበሳ መንገድ በህጋዊ አግባብ  እንዲከፈት የኤርትራ መንግስት ዝግጅቱን  እያጠናቀቀ መሆኑን  ከፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር ባደረጉት ውይይት ማረጋገጣቸውን ዶክተር ደብረፅዮን አስታውቀዋል።

ህጋዊ ስርዓት የተከተለ የመንገድ ግንኙነት እንዲኖር ፍላጎታቸው እንደሆነ አመልክተው የኢትዮጵያ መንግስት የተዘጋው መንገድን እንዲከፈት ጥረት በማድረግ ላይ እንዳለ እንደሚያውቁም አስረድተዋል፡፡

ይህም በሁለቱም ሃገራት ህዝቦች መካከል የተጀመረው ግንኙነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ገልጸዋል፡፡

"አሁንም የክልሉን ህዝብ አንድነቱን በማጠናከር  ሰላሙን ማስቀጠል ይጠበቅበታል" ያሉት ዶክተር ደብረጽዮን ህዝቡ ከጥርጣሬና ስጋት ወጥቶ የልማት ስራውን አጠናክሮ እንዲያከናውንም አሳስበዋል።

የክልሉ መንግስት ከህዝብ ጋር በመተባበር ደህንነቱን ለመጠበቅ  እንደሚሰራም  አስታውቀዋል።

ከኤርትራ ወደ ትግራይ ክልል ገብተው እየኖሩ ያሉ ዜጎችም በነፃነት እንዲቀሳቀሱና ሰርተው እንዲጠቀሙ የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም