ዘንድሮ ለሚካሄደው የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ሥራ ዝግጅት ተደርጓል– ምዕራብ ሸዋ ዞን

952

አምቦ ጥር 1/2011 በምዕራብ ሸዋ ዞን በዘንድሮው የበጋ ወራት በ156 ሺህ 456 ሄክታር መሬት ላይ የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ሥራ ለማከናወን የሚረዳ ዝግጅት መጠናቀቁን የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

በጽህፈት ቤቱ የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጥበቃና አጠቃቀም የሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ፈዬራ ኦሉማ ለኢዜአ እንደገለጹት የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ሥራው በተለዩ 529 ተፋሰሶች ላይ ይከናወናል። 

ጥር 20 ቀን 2011 ዓ.ም  በሚጀመረው የበጋ ወራት የአካባቢ ጥበቃ ልማት ሥራ እንዲካሔድባቸው ከተለዩት ተፋሰሶች መካከል በወረዳዎች ፍላጎት መሰረት  በ75 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የማሳና የጋራ ላይ ዕርከን ሥራ ይከናወናል።

እንደ አቶ ፈዬራ ገለጻ “ቀሪው የተራቆተ መሬትም ከሰውና ከእንስሳት ንክኪ ተከልሎ እንዲጠበቅ ይደረጋል” ብለዋል።

በልማት ሥራው 545 ሺህ 949 አርሶ አደሮች ይሳተፋሉ።

በሁሉም የገጠር ቀበሌዎች 19 ሺህ አርሶ አደሮች ስራውን እንዲመሩ ስልጠና የወሰዱ ሲሆን ለስራው የሚያስፈልጉ ዶማ ፣ አካፋና ሌሎች አነስተኛ የነፍስ ወከፍ የልማት መሳሪያዎች እንዲዘጋጁ ተደርጓል ።

የዞኑ አርሶ አደሮች በበኩላቸው  የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሥራው የሚያስገኘውን ጠቀሜታ በመረዳታቸው ዘንድሮ ከወዲሁ አስፈላጊው ዝግጅት ማድረጋቸውን ገልፀዋል ።

የጨሊያ ወረዳ አርሶ አደር ብርሃኑ ፉታሳ ባለፉት ዓመታት በአካባቢያቸው በተከናወኑ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሥራዎች የማሳቸው የአፈር ለምነት እየጨመረ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡

የመሬት ለምነት በመሻሻሉም ቀደም ሲል ከአንድ ሄክታር መሬት ያገኙት የነበረውን 25 ኩንታል የበቆሎ ምርት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በእጥፍ እንዳሳደገው ገልፀዋል፡፡

“ዘንድሮም ልማቱ የበለጠ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የበኩሌን እወጣለሁ” ብለዋል።

የደንዲ ወረዳ አርሶ አደር ጊዲሳ መንግስቱ በበኩላቸው ባለፉት ዓመታት በተሰራው የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ በአካባቢው ደርቀው የነበሩ ምንጮች መልሰው መፍለቃቸውን ተናግረዋል።

”ዘንድሮም ያለማንም ቀስቃሽና አስገዳጅነት በራሴ ፍላጎት ልማቱ እንዲጠናከር የድርሻዬን ለመወጣት ተዘጋጅቼአለሁ” ብለዋል።

በምዕራብ ሸዋ ዞን ለተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ሥራ ባለፉት ሰባት ዓመታት ትኩረት ተሰጥቶ በመሰራቱ ከ9 ሺህ ሄክታር በላይ የተራቆተ መሬት ማገገሙን ከዞኑ ግብርና ፅህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡