ተጠያቂነት የሰፈነበት አሰራር ለማጎልበት መገናኛ ብዙሀንና ምክር ቤቶች በቅንጅት ሊሰሩ ይገባል – የደቡብ ክልልም ምክር ቤት አፈ ጉባኤ

2451

ዲላ ግንቦት 18/2010 ግልፀኝነትና ተጠያቂነት የሰፈነበት አሰራር ለማጎልበት መገናኛ ብዙሀንና ምክር ቤቶች በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ የደቡብ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ሕይወት ኃይሉ ገለፁ ፡፡

“የዴሞክራሲ ተቋማት ግንባታና የሚዲያ ሚና” በሚል ርዕስ የምክር ቤት አባላትና የመገናኛ ብዙሃን አመራሮች በዲላ የምክክር መድረክ አካሂደዋል ፡፡

አፈ ጉባኤዋ ወይዘሮ ሕይወት ኃይሉ በምክክር መድረኩ ላይ እንደተናገሩት ምክር ቤቶች የህዝቡን ሁለንተናዊ  ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚበጁ ሕጎችን የማውጣት፣ ተግባራዊነታቸውን የመከታተልና የመቆጣጠር ሥልጣንና ኃላፊነት የተሰጣቸው የዴሞክራሲ ተቋማት ናቸው ፡፡

በተለይ በቋሚ ኮሚቴዎች አማካይነት የአስፈፃሚ አካላትን ተግባራት በመከታተልና በመቆጣጠር የህዝቡን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ምክር ቤቶች ከሚያከናውኗቸው ተግባራት በዋናነት ይጠቀሳሉ ፡፡

መገናኛ ብዙሀን ደግሞ የእነዚህን ኮሚቴዎች የግምገማ ውጤት ለህዝብ ጆሮ በማድረስ ዴሞክራሲያዊና ተጠያቂነት የሰፈነበት አሰራር እንዲጎለብት የማድረግ ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው አመልክተዋል፡፡

ዋና አፈ ጉባኤዋ በዚህ ረገድ መገናኛ ብዙሀንና በየደረጃው ያሉ ምክር ቤቶች በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል ፡፡

የመወያያ ሰነዱን ያቀረቡት የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ብሩክ ከበደ እንገለፁት በአንድ ሀገር ዴሞክራሲ ዕውን ለማድረግ የዴሞከራሲ ተቋማት ኃላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣት ይገባቸዋል፡፡

በተለይ ምክር ቤቶችና መገናኛ ብዙሀን ራሳቸውን ከአስፈፃሚ አካላት ተፅዕኖ በማላቀቅ የግልፀኝነትና ተጠያቂነት ባህል እንዲዳብር በጋራ ሊሰሩ አንደሚገባ አመልክተዋል ፡፡

“ይህን ለማድረግ መገናኛ ብዙሀን ለምክር ቤቶች ያላቸውን የተዛባ አተያይ ሊያስተካክሉ ይገባል” ብለዋል፡፡

በአንፃሩ የህዝብ ቀጥተኛ ውክልና ያላቸው ምክር ቤቶችም የሚዲያ ተቋማት ያለተፀዕኖ የሚሰሩበትን ምቹ ሁኔታ የመፍጠር ኃላፊነት እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡

በእስካሁኑ ሂደት “ቀዳሚ የዴሞክራሲ ተቋማት ናቸው” የሚባሉት በየደረጃው ያሉ ምክር ቤቶችና መገናኛ ብዙሃን ህገመንግስታዊ ኃላፊነታቸውን በተገቢው ባለመወጣታቸው የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲገነግኑ ምክንያት መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡

ከተሳታፊዎች መካከል የደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ሳሙኤል ወልደ ጊዮርጊስ በበኩላቸው “መገናኛ ብዙሀንና ምክር ቤቶች በዴሞራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ውስጥ አስፈፃሚ አካላትን የመፈተሸና የመጠየቅ ኃላፊነት አለባቸው” ብለዋል ፡፡

ከዚህ አኳያ በክልሉ ተጨባጭ ሁኔታ አጥጋቢ ሥራ እየተከናወነ እንዳልሆነ ተናግረዋል ፡፡

ተቋሙ ከክልሉ ፓርላማ ጋር እያከናወናቸው ያሉ ጅምር ተግባራት ቢኖሩም የህዝቡን ተጠቃሚነት በሚያረጋግጥ መልኩ ጥልቀጥ ያላቸው ሥራዎች አለመሰራታቸውን አስታውቀዋል ፡፡

የባለሙዎችን አቅም የማጎልበት፣ ከምክር ቤቱ ጋር ያለውን ትስስር የማጠናከርና ሌሎች የለውጥ ሥራዎችን በቀጣይ እንደሚሰሩም አስረድተዋል፡፡

የጌዴኦ ዞን ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፀሐይ ወረሣ የተቋማቱ የበጀትና የሰው ኃይል አቅም ውስንነት እንዲሁም በህግ የተሰጣቸውን ስልጣንና ኃላፊነት ተግባር ላይ ያለማዋል ዝንባሌ ምክር ቤቶችና መገናኛ ብዙሀን ያላቸውን ሚና እዳይጫወቱ እንቅፋት እንደሆነባቸው ገልፀዋል፡፡

“አክለውም በዴሞክራሲ ግንባታ ውስጥ ያለንን ጉልህ ድርሻ በአግባቡ ለመወጣት ቅንጅታዊ አሰራራችንን ማጠናከር ይገባናል” ብለዋል ፡፡

ላለፉት ሁለት ቀናት በተካሄደ የውይይት መድረክ “ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ የመገናኛ ብዙሃንና ምክር ቤቶች ሚና” የሚል ሰነድ ቀርቦ ውይይት ተካሂዶበታል፡፡