ነጻ የህግ አገልግሎቱ ችግራቸውን ለማቃለል እንደረዳቸው የሲናና እና ጎባ አካባቢ ነዋሪዎች ገለጹ

124

ጎባ ጥር 1/2011 የመዳ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ በሚሰጠው ነጻ የህግ አገልግሎት ችግራቸውን ለማቃለል እንደረዳቸው በባሌ ዞን ሲናና እና ጎባ አካባቢ  አስተያየታቸውን የሰጡ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡

ዩኒቨርሲቲው በሴቶች፣ በአካል ጉዳተኞችና አነስተኛ ገቢ ባላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ ትኩረት በማድረግ ነፃ የህግ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን አስታውቋል፡፡

ነዋሪዎቹ ለኢዜአ እንዳሉት  ዩኒቨርስቲው በሚሰጠው ነጻ የህግ አገልግሎት ተጠቃሚ መሆን ችለዋል፡፡

ከሲናና ወረዳ ነዋሪዎች መካከል  አቶ ታደሳ ሙልዕሳ   በጡረታ አበል ክፍያ መቋረጥ ምክንያት  ከፌዴራል የማህበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ የነበራቸው የመብት ጥያቄ ምላሽ ባለመግኘቱ ሲቸገሩ መቆየታቸወን ተናግረዋል፡፡

የመዳ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ በሚሰጠው ነጻ የህግ አገልግሎት ድጋፍ  ጉዳያቸው በህግ ባለሙያ ተይዞ በመከራከር ፍትህ ማግኘታቸውን አስታውቀዋል፡፡

ተቋርጦባቸው የነበረውን የጡረታ አበል በመደበኛነት እንዲያገኙ ከመደረጉም በላይ የሁለት ዓመት የተጠራቀመ ክፍያ  እንዲያገኙ በመደረጉ  መደሰታቸውንም ገልጸዋል፡፡

የጎባ ከተማ ቀበሌ አንድ ነዋሪ ወይዘሮ አለሚቱ ሁንዴ በበኩላቸው  ከዘመዶቻቸው ጋር በነበራቸው የመኖሪያ ቤት ይገባኛል ክርክር በገንዘብ ችግር ምክንያት  ጉዳያቸው መፍትሄ ሳያገኝ መቆየቱን አመልክተዋል፡፡

ሆኖም ዩኒቨርሲቲው በሰጠው ነጻ የህግ አገልግሎት ፍትህ በማግኘታቸው በቤታቸው ውስጥ  በነፃነት መኖር እንዲችሉ የተወሰነላቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ነፃ የህግ አገልግሎቱ  እሳቸውን ጨምሮ ሌሎችም የአካባቢው አቅመ ደካሞች  ፍትህ እንዲያገኙ አስተዋጽኦ እያደረገ  መሆኑን ወይዘሮ አለሚቱ ጠቁመዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው  የህግ ትምህርት ክፍል ዲን  አቶ ሰለሞን ግርማ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማሩ ሰራ በተጓዳኝ ማህበረሰብ ተኮር አገልግሎት እየሰጠ ነው፡፡ 

ተቋሙ በ2006 ዓ.ም. በሁለት ማዕከላት የጀመረው ነጻ የህግ አገልግሎት  በአሁኑ ወቅት ወደ አምስት ማዕከላት ከፍ ማድረጉን አመለክተዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው በሚሰጠው ነፃ የህግ አገልግሎት አቅመ ደካሞች፣አካል ጉዳተኞችና ከፍለው ጠበቃ የማቆም አቅም የሌላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ጨምሮ 6 ሺህ 443 ሰዎች ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡

በዚህም ተጠቃሚዎቹ ያወጡት የነበረውን ከግማሽ ሚሊየን ብር በላይ  ማስቀረት መቻሉን ዲኑ ተናግረዋል።

በተያዘው የበጀት ዓመትም አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ በሶስት ወረዳዎች  አዳዲስ ማዕከላትን በመክፈት ከ1 ሺህ ለሚበልጡ ተጠቃሚዎች ነጻ የህግ አገልግሎቱን እየተሰጠ መሆኑንም  አቶ ሰለሞን አመልክተዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የምርምር፣ የማህበረሰብ አገልግሎትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ስሜነህ ቤሴ በበኩላቸው  የአካባቢውን ማህበረሰብ ፍላጎት መሰረት ያደረጉ ከ50 የሚበልጡ ጥናትና ምርምሮች በማካሄድ ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡

ተቋሙ ከሚሰጣቸው ነፃ የህግ አገልግሎት መካከል  የምክር፣ ጥብቅና የማቆም፣ ክስ የመመስረት፣ የተለያዩ ሰነዶችንና ማመልከቻዎችን የማዘጋጀት ስራዎች ይገኙበታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም