የአየርላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር የኢትዮጵያ ጉብኝታቸውን ጀመሩ

83

አዲስ አበባ ጥቅምት 1/2011 የአየርላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ሊኦ ቫራድካር የኢትዮጵያ ጉብኝታቸውን ዛሬ ጀመሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ የሶስት ቀናት ጉብኝት ለማድረግ ትናንት ነው አዲስ አበባ የገቡት።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ባደረጉላቸው ግብዣ ወደ ኢትዮጵያ የመጡት የአየርላንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር አዲስ አበባ ሲገቡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ማርቆስ ተክሌ አቀባበል አደርገውላቸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ እና ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጋር ዛሬ ይወያያሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ለኢዜአ በላከው የጽሁፍ መግለጫ አስታውቋል።

አየርላንድ ኢትዮጵያ እያካሄደች ያለውን የኢኮኖሚ፣ ፖለቲካ እና ማህበራዊ እድገትና ለውጦች ከሚደግፉ የአውሮፓ አገራት ውስጥ ግንባር ቀደም እንደሆነች ይነገራል።

በአይሪሽ የልማት ተራድኦ አማካይኝነት ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ያደረጉ የልማት ፕሮጀክቶችን እንደምትደግፍና ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ እና በአካባቢው ሰላም እንዲሰፍን ለምታደርገው እንቅስቃሴ ድጋፍ እየሰጠች ትገኛለች።

ኢትዮጵያ እና አየርላንድ ረዥም ዘመን ያስቆጠረ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ያላቸው ሲሆን፣ አየርላንድ ኤምባሲዋን በ1986 ዓ.ም አዲስ አበባ ላይ ከፍታለች።

ኢትዮጵያም ኤምባሲዋን በ1995 ዓ.ም ጀምሮ በደብሊን በመክፈት ሁለቱ አገራት በትብብር በመስራት ላይ እንደሚገኙ ከቃል አቀባዩ ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የ39 ዓመቱ ፖለቲከኛ ሊኦ ቫራድካር ከሰኔ ወር 2009 ዓ.ም ጀምሮ አየርላንድን በጠቅላይ ሚኒስትርነት እያገለገሉ ይገኛሉ።

ሊኦ በ2009 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር ለመሆናቸው በፊት የአየርላንድ የትራንስፖርት ቱሪዝምና ስፖርት ሚኒስትር፣ የጤና ሚኒስትር፣ የማህበራዊ ጥበቃ ሚኒስትርና የቢዝነስ ተቋማትና ኢኖቬሽን ተጠባባቂ ሚኒስትር ሆነው ሰርተዋል።

ሊኦ ቫራድካር ከአየርላንድ ጠቅላይ ሚኒስትርነት በተጨማሪ ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ የአገሪቷ መከላከያ ሚኒስትርና የገዢው ፓርቲ ፋይን ጋኤል መሪ ሆነው በመስራት ላይ ሲሆኑ የአየርላንድ የታችኛው ምክር ቤት አባልም ናቸው።

አባታቸው ህንዳዊ እናታቸው ደግሞ አየርላንዳዊ የሆኑት ሊኦ ቫራድካር ወደ ፖለቲካ ህይወት የገቡት በ20 ዓመታቸው የሁለተኛ ዓመት የህክምና ዘርፍ ተማሪ በነበሩበት ወቅት በሚኖሩበት ሙድራት በተባለ አካባቢ በአካባቢያዊ ምርጫ ላይ በመሳተፍ ነበር።

የ39ኛ ዓመቱ ፖለቲከኛ ጥር 10 ቀን 2010 ዓ.ም 40 ዓመት የሚሞላቸው ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ልደታቸውን በሚያከብሩበት ጊዜ በፖለቲካው የቆዩበት ጊዜም 20 ዓመትን ይዛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም