ያለደረሰኝ ግብይት የሚፈፅሙ ህገ ወጥ ነጋዴዎች ላይ የተጠናከረ እርምጃ ሊወሰድ ይገባል

195

አዲስ አበባ ጥር 1/2011  በመዲናዋ ያለደረሰኝ  ግብይት  የሚፈፅሙ  ህገ ወጥ ነጋዴዎች ላይ የተጠናከረ እርምጃ  ሊወሰድ እንደሚገባ አንዳንድ ነዋሪዎች ተናገሩ።

የአዲስ አበባ ገቢዎች ባለስልጣን በበኩሉ ህብረተሰቡ  ያለ ደረሰኝ  ግብይት  የሚፈፅሙ  ህገ  ወጥ  ነጋዴዎችን ለባለስልጣኑ  በመጠቆም  ትብብር እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡

አስተያየታቸውን የሰጡ ነዋሪዎች እንደሚሉት  የተጠቃሚ  ማህበረሰብ  ግንዛቤ  አነስተኛ መሆን እና  የቁጥጥር  ስርዓቱ የላላ መሆን ችግሩን አባብሶታል፡፡

ከዚህ በፊት ደረሰኝ የመጠየቅ ባህላቸው አነስተኛ እንደ ነበር የተናገሩት የከተማዋ ነዋሪ አቶ ብሩክ አሰፋ፤ በደረሰኝ ግብይት መፈፀም ያለውን ፋይዳ ባለመረዳታቸው እንደሆነ ያስረዳሉ።

“ያለ ደረሰኝ  ግብይት  በምፈፅበት  ወቅት ተገቢ  ያልሆነ ክፍያ  ለመክፈል እገደድ ነበር” ያሉት አቶ ብሩክ  በደረሰኝ ግብይት መፈፀም ትክክለኛውን  ዋጋ  አውቆ  ለመግዛት  እና መንግስት መሰብሰብ የሚገባውን ግብር በአግባቡ እንዲሰበስብ ይረዳልም ይላሉ።

አሁን ለተጠቀሙበት አገልግሎትም ሆነ ለገዙት እቃ በደረሰኝ መገበያየት አገራዊ ግዴታቸውን እየተወጡ መሆኑን የገለጹት አቶ ብሩክ ህብረተሰቡ ደረሰኝ የመጠየቅ ባህሉን ማዳበር እና ደረሰኝ የማይሰጡ ህገ ወጥ ነጋዴዎችን ማጋለጥ ይኖርበታልም ብለዋል፡፡

መንግስት የሽያጭ መመዝገቢያ መሳሪያ ተጠቃሚ ሆነው ደረሰኝ የማይሰጡ ህገወጥ ነጋዴዎችና ተቋማት ወደ ህጋዊ መስመር እንዲገቡ እርምጃ መውሰድና  ማህበረሰቡም ደረሰኝ መቀበል አገራዊ ግዴታው መሆኑን የማስገንዘብ ስራ መስራት ይጠበቅበታል ብለዋል። ፡

አገልግሎት በሚጠቀሙበት እና የተለያዩ እቃዎች በሚገዙበት ወቅት ደረሰኝ  የመጠየቅ  ልምድ  እንዳላቸው የገለጹት አቶ ዘሪሁን ገረመው በበኩላቸው፤ አገልግሎት  ሰጪ  ተቋማት  ደረሰኝ  የመስጠት  ልምዳቸው አናሳ እንደሆነ እና አልፎ አልፎም ህጋዊ ያልሆነ ደረሰኝ እንደሚሰጧቸው ይናገራሉ፡፡

አቶ ዘሪሁን እንደሚሉት የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ደረሰኝ በማይቆርጡ  ነጋዴዎች ላይ የሚያደርጉት ቁጥጥርና የሚወሰደው እርምጃ  አናሳ  በመሆኑ አገሪቱ  ማግኘት የሚገባት ገቢ እያጣች ነው።  

ህብተሰቡን ባሳተፈ መልኩም ህጋዊ ደረሰኝ የማይቆርጡ የንግድ ተቋማት እና ነጋዴዎችን በመለየት የማስተካከያ እርምጃ ሊወሰድባቸው እንደሚገባም ተናግረዋል።  

በኮንስትራክሽን  እቃዎች  መሸጫ  የንግድ ዘርፍ  የተሰማሩ  አቶ አውራሪስ  መከተ በበኩላቸው በደረሰኝ ግብይት የማይፈፅሙ ነጋዴዎች የንግዱን  ስርዓት እያናጉ ነው ብለዋል።

ሸማቹ ደረሰኝ  ከሚሰጡ  የንግድ  ተቋማት  ላይ ከመግዛት ይልቅ ያለደረሰኝ  የሚሸጡ የንግድ ተቋማትን ይመርጣል ያሉት አቶ አውራሪስ፤  ተጨማሪ እሴት ታክስ እየተከፈለ በደረሰኝ መሸጥ፤  ደረሰኝ ከማይሰጡ ተመሳሳይ ምርት ከያዙ ንግድ ተቋማት ጋር መወዳደር  ስለማይችሉ እሳቸውም ያለደረሰኝ እየሸጡ መሆኑን ተናግረዋል። 

ህጉን ተከትሎ ህበረተሰቡ ለተገለገለበት እና ለገዛው እቃ ደረሰኝ  የሚሰጡ  ነጋዴዎች በህገ  ወጥ መንገድ ግብይት  በሚፈፅሙ  ነጋዴዎች ምክንያት  ከንግድ ወድድሩ  ውጪ እየሆኑ  ነው ይላሉ።

ችግሩን በመፍታትና የተረጋጋ  የንግድ  ስርዓት በመፍጠር  የአገሪቱ  ኢኮኖሚ  የሚያመነጭውን ገቢ በሙሉ ለመሰብሰብ  መንግስት በህገ ወጥ ነጋዴዎች ላይ የሚያደርገውን ቁጥጥር ና እርምጃ  ማጠናከር እንደሚገባም ተናግረዋል። 

በአዲስ አበባ ከተማ  ገቢዎች ባለስልጣን  የሽያጭ  መመዝገቢያ አጠቃቀም  እና ቁጥጥር  ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር  አቶ ተስፋዬ ነጋሽ የሽያጭ  መመዝገብያ  መሳሪያን  በአግባቡ የማይጠቀሙ ግብር  ከፋዮች  አስተዳደራዊ  እና ህጋዊ እርምጃ  እየተወሰደባቸው   ነው ብለዋል፡፡

በዚህም  በተያዘው  በጀት ዓመት  ብቻ  በ49 ሺ 184 የንግድ  ቤቶች   በተደረገው ዳሰሳ 1 ሺ 111 የንግድ ቤቶች ያለ  ደረሰኝ  ግብይት  ሲፈፅሙ ተገኝተው  እስከ  ሃምሳ ሺህ ብር የሚደርስ  ቅጣት ተጥሎባችዋል ብለዋል፡፡

በታክስ  አዋጁ  መሰረት  የሽያጭ  መመዝገቢያ ተጠቅመው በደረሰኝ  መገበያየት የሚጠበቅባቸው  የንግድ ቤቶች  ያለደረሰኝ  ግብይት  መፈፀም  ያለውን  የህግ  ተጠያቂነት  አውቆ ህጋዊ መንገድ እንዲከተሉም አሳስበዋል፡፡

በደረሰኝ  መገበያየት ያለውን ጥቅም ለህብረተሰቡ  የግንዛቤ ማስጨበጫ  ስራዎች እየተከናወነ  መሆኑን የተናገሩት አቶ ተስፋዬ ህብረተሰቡም  ያለ ደረሰኝ  ግብይት  የሚፈፅሙ  ህገ ወጥ ነጋዴዎችን  ለባለስልጣን  መስሪያ ቤቱ በመጠቆም  ሃላፊነቱን እንዲወጣ  ጠይቀዋል፡፡

የህብረተሰቡን በደረሰኝ የመገበያየት ባህል ለማበረታታት የሚስችል በደረሰኝ ወረቆቶች 

ላይ የሎተሪ ዕጣ ተሸላሚ የሚያደርግ  ፕሮግራም በቅርቡ  እንደሚጀመርም  ተናግረዋል።

ዓመታዊ ሽያጫቸው ከ500 ሺ በታች የሆኑት የደረጃ ‘ሀ’ እና ‘ለ’ ግብር ከፋዮች የሽያጭ መመዝገቢያ  መሳሪያ እንዲይዙ የሚጠበቅባቸው ሲሆን የፋናንስ ተቋማት እና ማዲያዎችን ሳይጨምር በከተማዋ ካሉት 119 ሺ 155  ግብር ከፋዮች 102 ሺ ያህሉ የሽያጭ መመዝገቢያ መሳሪያ  ለመያዝ ይገደዳሉ፡፡

እስካሁን  መሳሪያውን  በማስገባት አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙ ግብር ከፋዮች 90 ሺ 611 ብቻ  እንደሆነም  ዳይሬክተሩ  ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም