በአርባ ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባው ትምህርት ቤት ተመረቀ

63

አዲስ አበባ ታህሳስ 30/2011 አል ማክቱም ፋውንዴሽን የተባለ የተባበሩት አረብ ኤምሬት ግብረ ሰናይ ድርጅት በአርባ ሚሊዮን ብር ወጪ ያስገነባው ትምህርት ቤት ዛሬ ተመረቀ።

ግብረ ሰናይ ድርጅቱ እስከ አሁን በኢትዮጵያ አራት ትምህርት ቤቶችን አስገንብቷል።

ትምህርት ቤቱ በየካ ክፍለ ከተማ በተለምዶ አያት አደባባይ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የሚገኝ ሲሆን የአፍ መፍቻ ቋንቋቸው አፋን ኦሮሞ የሆኑ ተማሪዎች የሚማሩበት ነው።

የትምህር ቤቱ የግንባታና የቁሳቁስ ወጪ በግብረ ሰናይ ድርጅቱ የተሸፈነ ሲሆን ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት የአስተማሪዎችን ሙሉ የደመወዝ ክፍያም በድርጅቱ የሚሸፈን ይሆናል።

ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ በትምህርታቸው የላቀ ውጤት ለሚያመጡ ተማሪዎችም ሱዳን በሚገኘው 'ኢንተርናሽናል ፎር አፍሪካ' በተሰኘው ዓለም አቀፍ ትምህርት ቤት የነፃ የትምህርት ዕድል ተጠቃሚ እንደሚሆኑም የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ታቦር ገብረመድህን በምርቃት ስነ ስርዓቱ ላይ ተናግረዋል።

በተጨማሪም ለመምህራን የትምህርት ዕድል ለመስጠትና ከሌሎች የአፍሪካ አገራት ጋር የመምህራን የልምድ ልውውጥ ለማድረግ መታቀዱንም ጠቁመዋል።

የትምህርት ቤቱን የቅበላ አቅም ለማሳደግ የማስፋፊያ ስራ ለመስራት ዝግጅት መጠናቀቁንም ዶክተር ታቦር ተናገረዋል።

የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር ከድር ጃርሶ በበኩላቸው ትምህርት ቤቱ የአፍ መፍቻቸው አፋን ኦሮሞ ለሆኑ እና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ወላጆች ልጆች የትምህርት ዕድል ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው ብለዋል።

እንዲሁም ትምህርት ቤቱ በአካባቢው መከፈቱ ለበርካታ ሥራ አጥ ኢትዮጵያውያን የስራ ዕድል የፈጠረ መሆኑንም ገልጸዋል።

የአል ማክቱም ፋውንዴሽን የኮሙኒኬሽን ባለሙያ አቶ አብዱልሸኩር መንዛ እንዳሉት ግብረ ሰናይ ድርጅቱ በኢትዮጵያ የትምህርት ዘርፍ የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ በማጠናከር በሌሎች ዘርፎች ለመስራትም ዕቅድ አለው።

ግብረ ሰናይ ድርጅቱ በኢትዮጵያ የትምህርት ዘርፍ መጠናከር የአገሪቱ መንግስት ላደረገው ቀና ትብብርም  አቶ አብዱልሸኩር አመስግነዋል።

አል ማክቱም ፋውንዴሽን በየካ ክፍለ ከተማ ካስገነባው ትምህርት ቤት በተጨማሪ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማም በተመሳሳይ የአፍ መፍቻ ቋንቋቸው አፋን ኦሮሞ የሆኑ ተማሪዎች የሚማሩበት ትምህርት ቤት አስገንብቷል።

በሁለቱም ክፍለ ከተሞች የተገነቡት ትምህርት ቤቶች በአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ስር እንዲተዳደሩ የኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ አስረክቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም